
#አቡነ_ሀብተ_ማርያም (ስንክሳር) ➯ዳግመኛም በዚህች ቀን ቅዱስ አባታችን አቡነ ሀብተ ማርያም ፅንሰታቸው ነው። አባታቸው ፍሬ ቡሩክ እናታቸው ዮስቴና የሚባሉ በሕገ እግዚአብሔር፣ በሃይማኖት፣ በትሩፋትና በምግባር ጸንተው የሚኖሩ ደጋግ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ ቅዱስ አባታችን ፅንሰታቸው ነሐሴ 26፣ ልደታቸው ግንቦት 26፣ ዕረፍታቸው ኅዳር 26 ነው፡፡ አቡነ ሀብተ ማርያምን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ‹‹አምስት መቅሰፍታት እንዲጠፉ በደጄ በደብረ ሊባኖስ ተቀበርልኝ›› ብለው የለመኗቸው ታላቅ አባት ናቸው፡፡ ➯የአቡነ ሀብተ ማርያም እናት ቅድስት ዮስቴና ጻድቁ አቡነ ሀብተ ማርያምን ከመውለዷ በፊት ‹‹ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢገዛ ነፍሱን ካጣ ምን ይጠቅመዋል?›› የሚለውን የወንጌል ቃል አስባ መንና ወደ በረሃ የገባች ቢሆንም በበረሃ ውስጥ ከሰው ተለይቶ የሚኖር የበቃ ባሕታዊ በዋሻ ውስጥ አገኘችና ለምነና ወደ በረሃው እንደመጣች ነገረችው፡፡ ባሕታዊውም በጸሎት ወደ እግዚአብሔር ካመለከተ በኋላ ‹‹ምንኩስና ለአንቺ አልተፈቀደልሽም፣ ወደ ቤትሽ ግቢ፣ ከሕጋዊ ባልሽ ወንድ ልጅ ትወልጃለሽ እርሱም ለዓለም ሁሉ የሚጠቅም፣ ሰው ሁሉ የሚማፀነው፣ ገድሉ ትሩፋቱ በዓለም የሚነገርለት፣ በነፍስም በሥጋም የሚያማልድ፣ እንደ መልአክትም ክንፈ ጸጋ የሚሰጠው በምድር ሆኖ መንበረ ጸባኦትን የሚያይ ወንድ ልጅ ትወልጃለሽ›› በማለት ትንቢት ከነገራት በኋላ ቅድስት ዮስቴና ወደ ቤቷ ተመለሰች፡፡ እርሷም ሀብተ ትንቢት እስከመሰጠት ድረስ የደረሰች በሃይማኖት በምግባር በትሩፋት ያጌጠች ሆነች፡፡ ➯ቅድስት ዮስቴናም ወደ ቤቷ ከተመለሰች በኋላ አቡነ ሀብተ ማርያም ተወለዱና ወላጆቻቸው ፈሪሃ እግዚአብሔርን እያስተማሩ አሳደጓቸው፡፡ ከዕለታት በአንድ ቀን ካህናቱ በቤተ ክርስቲያን ምህላ ሲያደርሱ ‹‹እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ›› እያሉ ሲጸልዩ ሰምተው በልቡናቸው ‹‹ይህች ጸሎት በጣም ጥሩ መልካም ጸሎት ናት፤ እኔ ይህችን ጸሎት መርጫታለሁ፤ በዚህ ጸሎት ዓለም ከአሳችነት ኅሊና በሚመጣውም ዓለም ከገሃነም እሳት እንድንድንባት አውቃለሁ›› አሉ፡፡ ይህችንም ጸሎት ማዘውተር ጀመሩ፡፡ እናትና አባታቸውም በተኙ ጊዜ ሌሊት ለጸሎት ተነሥተው በዚህ ጸሎት ፈጣሪአቸውን ያመሰግኑ ነበር፤ ስግደትን ይሰግዳሉ ነገር ግን እናትና አባታቸው ከእንቅልፋቸው በነቁ በጊዜ ሮጠው ወደ መኝታቸው ሄደው ይተኛሉ፡፡ የጽድቅ ሥራቸውንም ከአምላካቸው በቀር ማንም አያውቅባቸውም ነበር፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ አባታቸው ፍሬ ብሩክ የበግ ጠባቂ አደረጋቸው፡፡ እግዚአብሔር ግን በኋላ ለብዙዎች ስውራን ቅዱሳንና በዓለም ለሚኖሩ ምዕመናን በጎች ጠባቂ ያደርገው ዘንድ ወዶ መርጦታልና ያ ቀን እስኪደርስ ድረስ ፈጣሪያችን አቡነ ሀብተ ማርያምን ይጠብቃቸው ነበር፡፡.........