አቡነ_ኢየሱስ_ሞዐ (ስንክሳር) ➯በዚህች ቀን አባታቻን አቡነ ኢየሱስ ሞዐ የተፀነሱበት ዕለት ነው፡፡ ቅዱሱ… — "፩ እምነት" ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ Channel — TG.ME

#አቡነ_ኢየሱስ_ሞዐ (ስንክሳር)

➯በዚህች ቀን አባታቻን አቡነ ኢየሱስ ሞዐ የተፀነሱበት ዕለት ነው፡፡ ቅዱሱ አባት ሀገራቸው ጎንደር ክፍለ ሀገር ስማዳ ወረዳ ሲና ዳኅና በሚባል ቦታ ነሐሴ 26 ቀን ተፀንሰው ግንቦት 26 ቀን 1210 ዓ.ም ከአባታቸው ዘክርስቶስና ከእናታቸው እግዚእ ክብራ ተወለዱ። የተወለዱትም በቅዱስ ነአኲቶ ለአብ ዘመነ መንግስት ነው፡፡ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት የቆብ አባት ሲሆኑ ታላቁን ሐይቅ ቅዱስ እስጢፋኖስን ገዳም የቆረቆሩ ደገኛ አባት ናቸው፡፡

➯ዕድሜያቸው 30 ዓመት እስከሚደርስ ድረስ ከቤተሰቦቻቸው ትምህርተ ሃይማኖትንና ግብረ ገብን ሲማሩ ከቆዩ በኋላ በ1240 ዓ.ም ይህንን ዓለም በመተው ወደ ደብረ ዳሞ ገዳም ገቡ፡፡ በደብረ ዳሞ ገዳም መነኰሳቱን እየረዱ፣ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት እያጠኑ፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን እየገለበጡ ለሰባት ዓመታት ከቆዩ በኋላ የደብረ ዳሞ 3ኛ አበ ምኔት ከሆኑት ከአባ ዮሐኒ እጅ ምንኩስናን በ1247 ዓ.ም ተቀበሉ፡፡

➯አንድ ቀን ሌሊት መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ወደርሳቸው መጥቶ ‹‹የስምህ መክበርያ ወደሆነው ሐይቅ ወደ ተባለው ሥፍራ ሂድ›› አላቸው፡፡ አባታችንም ‹‹ቦታውን እንዴት ዐውቀዋለሁ?›› በማለት መልአኩን ቢጠይቁት ‹‹ተነሥ! ጉዞህን ጀምር ቦታውን እኔ አሳይሃለሁ›› አላቸው፡፡ አባ ኢየሱስ ሞዓ በመልአኩ እንደታዘዙት ከበዓታቸው ተነሥተው ተከተሉት፡፡ የብዙ ወራት መንገድ የሆነውን ጐዳናም በስድስት ሰዓት አደረሳቸው፡፡ በዚያን ወቅት ከሐይቅ ገዳም በስተ ሰሜን ወደነበረው ጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን ደረሱ፡፡ ወደ ሐይቅ እስጢፋኖስ ከመግባታቸው በፊት ለ6 ወራት ያህል በጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን አገልግለዋል፡፡ ያገለግሉበት በነበረው ቤተ ክርስቲያን ቀን ቀን ሕዝቡን ሲያስተምሩ በመዋል ሲመሽ ወደ ሐይቁ በመግባት ሲጸልዩ ያድሩ ነበር፡፡ በሐይቅ እስጢፋኖስና በዙርያው ለነበሩ አበውም ማታ ማታ አንድ ብርሃን ወደ ሐይቁ ሲገባ ጠዋት ጠዋትም ሲወጣ ይታያቸው ነበር፡፡ ከዚህም በኋላ አባታችን በገዳሙ አባቶች ልመናና በልዑል እግዚአብሔር ትዕዛዝ ወደ ሐይቅ ገዳም ገብተው አበምኔት ሆኑ፡፡........
September 1, 2026 36