.....➯በአንደኛውም ቀን አቡነ ሀብተ ማርያም ከሌሎች ቅዱሳን ጋር ሆነው ሲሄዱ ብዙ አጋንንት እየተደነባበሩ ወደ ታች ሲወርዱ ተመለከቱና አባታችን ሥራቸውን ለማየት ተከተሏቸው፡፡ አንዱንም ኃጥእ ይዘው ነፍሱን ከሥጋው ለዩዋትና ወደ ሲኦል አወረዷት፡፡ አባታችንም ከሌሎቹ ቅዱሳን ጋር ሆነው ያችን ነፍስ ይምርላቸው ዘንድ ጌታችንን በጸሎት ማለዱት፡፡ ነገር ግን ‹‹ለጣዖት ስትሰግድ ስለኖረች ይህችን ነፍስ አልምራትምና አትድከሙ›› የሚል ቃል ከልዑል እግዚአብሔር ዘንድ መጣላቸው፡፡ ቅዱሳኑም ‹‹ልመናችንን የማትቀበል ከሆነ በከንቱ ሰብስበኸናል›› ብለው ቢያዝኑ እግዚአብሔርም ‹‹ሕገ እግዚአብሔርን የዘነጉ ሰዎችን ቅጣት እንድታዩ ነው›› አላቸው፡፡ እነርሱም ሕገ እግዚአብሔርን የዘነጉ ሰዎችን ሲቀጣቸው ለደጋጎቹ ሰዎች ደግሞ መልካሙን ዋጋቸውን ሲሰጣቸው አይተው አንድ ሆነው አመስግነውታል፡፡
➯ከዚህም በኋላ መልአኩ ቅዱስ ራጉኤል አንዱን ሰው በመብረቅ ቀሰፈውና ቅዱስ ሚካኤል ሄዶ ቅዱስ ራጉኤልን ሲከራከረው አባታችን ተመለከቱ፡፡ ቅዱስ ሚካኤል ‹‹የእኔ አገልጋይ ነውና ለምን ገደልከው?›› ሲለው ቅዱስ ራጉኤልም ‹‹ሰንበት ሳይለይ ዝሙትን መሥራት የለመደ ሥራውም ዝሙት ስለሆነ በፈጣሪዬ ታዝዤ ነው የገደልኩት፡፡ ኃጥአንን ሊያጠፋ እንጂ ጻድቃንን ለመቅጣት መብረቅ እንዳይታዘዝ አንተስ ታውቅ የለም እንዴ?›› አለው፡፡ ይህንንም ተባብለው ከሥላሴ ፊት ሰግደው ቅዱስ ሚካኤል የተገባለትን ቃልኪዳን በማሳሰብ ምልጃውን አቀረበ፡፡ እግዚአብሔርም በጎና ክፉ ሥራዋን ባስመዘነ ጊዜ በጎ ሥራዋ ስለበለጠ ቅዱስ ሚካኤል ያችን ነፍስ ታቅፎ ወስዶ ለቅዱስ ገብርኤል ሰጠው፡፡ ሰባቱም ሊቃነ መላእክት እየተቀባበሉ ወስደው ከመስቀል ዘንድ አደረሷት፡፡ ለቅዱስ መስቀልም ካሰገዷት በኋላ አሳልመዋት በቅዱስ ሚኤካል አማላጅነት ወደ ገነት አስገቧት፡፡ አቡነ ሀብተ ማርያምም ይህን በተመለከቱ ጊዜ ቅዱስ ሚካኤልን ‹‹መስቀል ታሳልሟት ዘንድ ያችን ነፍስ ወደ መስቀል ለምን ወሰዳችኋት?›› ብለው ጠየቁት፡፡ መልአኩም ‹‹በትልቅም በትንሽም ነገር ክርስቲያናዊትን ነፍስ የሚቃወም ቢመጣባት ድል የምትነሳበትን በመስቀል ፍርድ ይታይላታልና ስለዚህ ነው፡፡ የሚከራከራት ቢኖር ግን እንዳየኸው ወደ መስቀል ባደረሷት ጊዜ የሚቃወማት ሰይጣን ፈጥኖ ይርቅላታል ዳግመኛም ሊከራከራት አይችልም›› አላቸው፡፡
➯ከአቡነ ሀብተማርያም በረከት ለመቀበል ብዙ ቅዱሳን ከሮም፣ ከግብፅ፣ ከአስቄጥስና ከሲሐት ገዳም ወደ አባታችን ዘንድ ይመጡ ነበር፤ ከየሀገራቸውም በአንበሳ ተቀምጠው የሚመጡ አሉ፤ ክንፍ ተሰጥቷቸው እንደ ንስር የሚበሩም አሉ፤ ብፁዕ አቡነ ሀብተ ማርያምም የቅዱሳኑን ብቃት አይተው ‹‹ሥራችሁ እንዲህ እንዲህ ሲሆን ለምን ወደኔ መጣችሁ?›› ብለው ሲጠይቋቸው ቅዱሳኑም ‹‹በማንኛውም ሥራ እግዚአብሔርን በለመነው ጊዜ በኢትዮጵያ የሚኖር እንደ ሙሴ ያለ ሀብተ ማርያም የሚባል ወዳጄ አለና ሁሉን ስለሚነግራችሁ ዘወትር እርሱን ጠይቁ ብሎ ስላዘዘን ወደ አንተ መጣን›› አሏቸው፡፡ አባታችንም ቅዱሳኑን ከባረኳቸውና ከእነርሱም ከተባረኩ በኋላ አባታችን ለቅዱሳኑ የሚመጣውን እንዳለፈ የሚደረገውንም እንደተደረገ አድርገው ይነግሯቸዋል፡፡ ቅዱሳኑም ከልጅነታቸው ጀምረው እስከዚያች ቀን ድረስ የሠሩትን ሥራ ሁሉ ይነግሯቸዋል፡፡ እነርሱም እጃቸውን እየሳሙ በረከታቸውን ይቀበሉ ነበር፡፡ እንደዚሁም አቡነ ሀብተ ማርያም ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል እየተራዱዋቸው ቀድሰው በሚያቆርቡ ጊዜ ተሰውረው የሚኖሩ 500 ስውራን ቅዱሳን መጥተው ሥጋ ወደሙን ከአባታችን እጅ ተቀበሉ፡፡ ቀድሰውም ወደበዓታቸው እንደገቡ እመቤታችን ተገልጣላቸው ‹‹በነገውም ዕለት ቅዳሴዬን ቀድስ፣ ይህም ቅዳሴ መዓዛ ቅዳሴ ነውና፡፡ የዓለም መሠረት ማርያም ወደኔ ነይ ብለህ በጠራኸኝ ጊዜ ነቢያትን ሐዋርያትን አስከትዬ መጥቼ እባርክሃለሁ›› አለቻቸው፡፡ አባታችንም ‹‹በነገው ዕለት ሌላ ተረኛ ቄስ ይቀድሳልና ይህ እንዴት ይሆንልኛል?›› አሏት፡፡ እመቤታችንም ‹‹ፈቃዴ ስለሆነ አንተ እንድትቀድስ አደርጋለሁ›› አለቻቸው፡፡ በነጋታው ተረኛው ቄስ ከእንቅልፉ በነቃ ጊዜ ቸኩሎ እየተፋጠነ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲገሰግስ ወድቆ ጥርሱ ደማና ስለ ሥጋ ወደሙ ቅዳሴ እጅግ ደንግጦ ወደ አባታችን መጥቶ ‹‹ቅዳሴው በእኔ ስም ከሚታጎል አንተ ቀድስልኝ›› አላቸው፡፡ አባታችንም አስቀድማ እመቤታችን የነገረቻቸውን ነገር አስበው እያደነቁ ሄደው ቀደሱ፡፡ እመቤታችንም ነቢያትን ሐዋርያትን አስከትላ መጥታ ባረከቻቸው፡፡
➯ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
#ስንክሳር ነሐሴ 26 እና #ከገድላት_አንደበት
September 1, 2026 74