መልአኩ ቅዱስ ሚካኤልም አባታችንን እንደ ጓደኛ ሆኖ ዘወትር ይጎበኛቸው ነበር፡፡ ቅዱሳን አባታቸንን ሊጎበኟቸው… — "፩ እምነት" ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ Channel — TG.ME

....➯መልአኩ ቅዱስ ሚካኤልም አባታችንን እንደ ጓደኛ ሆኖ ዘወትር ይጎበኛቸው ነበር፡፡ ቅዱሳን አባታቸንን ሊጎበኟቸው መጥተው ከደጅ ቆመው እንደሆነ ቅዱስ ሚካኤል አባታችንን ‹‹እከሌ ጉዳዩ እንዲህ ነው እንዲህ ብለህ ተናገረው…›› እያለ ያማክራቸው ነበር፡፡ እሳቸውም ቅዱስ ሚካኤል ካዘዛቸው በቀር ምንም አይሠሩም ነበር፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትንም ባነበቡ ጊዜ ኃይለ ቃሉን እየተረጎመ ምሥጢራትን ይነግራቸዋል፤ የተሰወረውንም ይገልጥላቸዋል፡፡ ከእንስሳት ጩኸት ጀምሮ ከዱር አራዊት ድምፅና እስከ አእዋፍ ቋንቋ ያለውን ያስረዳቸው ነበር፡፡

➯ይኸውም መልአክ አንድ ቀን አቡነ ሀብተ ማርያምን ወደ ቤተ ክርስቲያን አስገብቷቸው ሥጋ ወደሙን ለመቀበል ተዘጋጅተው ሳለ ወንጌል የሚነበብበት ሰዓት ሲደርስ ያልተማረ ቄስ የክርስቶስ ጌትነቱን የምትናገር ወንጌልን ሲያነብ ‹‹ወዮሴፍ ብእሲሃ ለማርያም ጻድቅ ውእቱ›› የሚል ከቄሱ አፍ ይህን ንባብ አባታችን ሲሰሙ እጅግ ደንግጠው ወንጌል ወደሚነበብበት ስፍራ ሄደው የሚያነበውን ቄስ ገሠጹት፡፡ ‹‹ወዮሴፍሰ ፈሃሪሃ ለማርያም ጻድቅ ውእቱ በል እንጂ ብእሲሃ አትበል›› ብለው መከሩት፡፡ ቄሱም አቡነ ሀብተ ማርያም እንዳዘዙት ከስህተቱ ወደ ቀና ንባቡ ተመለሰ፡፡ ይህን ጊዜ ጌታችን ለአባታችን ድጋሚ ተገልጦላቸው ‹‹ሀብተ ማርያም ሆይ ይህን ትምህርትህን ወድጄ አመሰገንኩህ፣ የእናቴን የድንግል ማርያምን የድንግልናዋን ንጽሕና ስለ አከበርክ እኔም በመንግስተ ሰማያት ፈጽሜ አከብርሃለሁ›› አላቸው፡፡ ዳግመኛም ጌታችን ‹‹አሁንም ዮሴፍ ብእሲሃ ለማርያም የሚሉትን ሁሉ ለያቸው እንጂ አትተዋቸው፤ እንዲህ የሚል ጽሑፍም ብታገኝ እንዳይኖር እርሱን ፍቀህ ፈሃሪሃ ለማርያም የሚለውን ጻፍ›› ብሎ አባታችንን ካዘዛቸው በኋላ ሰላምታ ሰጥቷቸው ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡ አባታችንም በዚህ ጊዜ ፊታቸው ላይ ብርሃን ስለተሳለባቸውና እንደ ፀሐይ ስላበራ ሰዎችም አይተው ባደነቁ ጊዜ ወደ በዓታቸው ገቡና ጌታችንን ‹‹አቤቱ ጌታዬ ሆይ በሰው ፊት ክብሬን አትግለጥብኝ ሰውርልኝ፣ በቸርነትህም አድነኝ›› ብለው ጸለዩ፡፡ እንዲህም ብለው በጸለዩ ጊዜ ፊታቸው መልኩ ተለውጦ እንደ ቀድሞው ሆነ፡፡

➯ከዕለታትም በአንደኛው ቀን አባታችን ታመው ተኝተው ሳለ ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳውሎስ መጥተው ሥጋ ወደሙን አቀብለዋቸዋል፡፡፡ አባታችን በጸሎት ላይ ሳሉ ቅዱስ ሚካኤል ነጥቆ ወደ ሰማይ ወስዶ ቅዱሳን የሚኖሩባቸውን ዓለማት፣ መንግስተ ሰማያትን እንዲሁም ኃጥአን የሚኖሩበትን ሲኦልን አሳያቸው፡፡ በገነት ያሉትንም ከአዳም ጀምሮ እሳቸው እስካሉበት ጊዜ እስከ አቡነ መርሐ ክርስቶስ ድረስ ያሉትን ቅዱሳን አሳያቸው፡፡ ከዚህም በኋላ በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት ቆመው ሳለ ሰይጣንም መጥቶ በእግዚአብሔር ፊት ቆመና ‹‹አቤቱ ጌታዬ ሆይ በሀብተ ማርያም ላይ እንደ ኢዮብ ብዙ መከራ አጸናበት ዘንድ ፍቀድልኝ›› ብሎ እየጮኾ ሲናገር አባታችን እጅግ ፈርተው አለቀሱ፡፡ እግዚአብሔር ግን በሰይጣን ላይ ተቆጥቶ ‹‹በነፍሱም በሥጋውም መከራ ታጸናበት ዘንድ አልፈቅድም›› አለው፡፡ ‹‹እኔ ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ መርጨዋለሁና በንጽሕናና በቅድስና ኃጢአት እንዳይሠራ ዘወትር እጠብቀዋለሁ፤ በእርሱ ላይ ማሰልጠንስ ይቅርና በሀብተ ማርያም ጸሎት በተማጸነኝ ሁሉ ላይ እንኳን አላሠለጥንህም›› አለው፡፡ ሰይጣንም ይህን ቃል ሰምቶ አፍሮ እያዘነ ሄደ፡፡

➯አቡነ ተክለ ሃይማኖትም ከእርሳቸው በኋላ በመንበራቸው ከተሾሙት ከስምንቱ መምህራን ጋር ለሀብተማርያም ተገለጡላቸው፡፡ እነርሱም ኤልሳዕ፣ ፊሊጶስ፣ ሕዝቅያስ፣ ቴዎድሮስ፣ ዮሐንስ፣ ዮሐንስ ከማ፣ እንድርያስና መርሐ ክርስቶስ ናቸው፡፡ እነዚህም መልካቸው እንደ ፀሐይ ያበራ ልብሳቸው እንደ መብረቅ ያንጸባርቅ ነበር፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖትም ልብሳቸው የእሳት ላንቃ የከበበው መልኩም ነጭ የሆነ የሚያስደንቅ ሆኖ ‹‹በቅድምና ለነበረ ለአብ በቅድምና ለነበረ ለወልድ በቅድምና ለነበረ ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይገባል›› እያለ ልብሳቸው በሰው አንደበት ያመሰግን ነበር፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖትም አቡነ ሀብተ ማርያምን ‹‹ልጄ ሀብተ ማርያም ሆይ! ፈጣሪዬ እግዚአብሔር ስለወደደህ ብዙ ምርኮ እንዳገኘህ በአንተ ፈጽሞ ደስ ይለኛል፡፡ ነገር ግን የምለምንህ ነገር አለና እሺ በለኝ›› አሏቸው፡፡

➯አቡነ ሀብተ ማርያምም ‹‹ጌታዬ ነገሩ ምንድን ነው?›› ሲሏቸው አቡነ ተክለሃይማኖት ‹‹ከተቀበርኩበት ቦታ እንድትቀበር ቃል ኪዳን ግባልኝ›› አሏቸው፡፡ አቡነ ሀብተማርያምም ‹‹አባቴ ሆይ ይህንን አደርግ ዘንድ ስለምን ትወዳለህ?›› አሏቸው፡፡ አቡነ ተክለሃይማኖትም በሀገሬ ላይ የታዘዙ አምስት መቅሰፍቶች አሉና ስለዚህ ነው እነዚህም አንዱ መብረቅ ነው፤ ሁለተኛውም ቸነፈር ነው፤ ሦስተኛውም ረሃብ ነው፤ አራተኛውም ወረርሽኝ ነው፤ አምስተኛውም የእሳት ቃጠሎ ነው፡፡ የአንተ አጽም በውስጡ የተቀበረ እንደሆነ አጥንቴ የተቀበረባት ሀገሬ ከነዚህ መቅሰፍታት ትድናለች›› አሏቸው፡፡

➯አቡነ ሀብተ ማርያምም ‹‹ንዑድ ክቡድ የምትሆን አባቴ ሆይ ልዩ ክቡር በሚሆን በአንተ አጽም መቀበር ያልዳነች በእኔ አጽም መቀበር ድኅነት ታገኛለችን? ይህንስ ተወው›› ብለው በተከራከሯቸው ጊዜ አቡነ ተክለ ሃይማኖትም መልሰው ‹‹ልጄ ሀብተ ማርያም ሆይ አንተ የማታውቀው ከፈጣሪያችን ከእግዚአብሔር የተሰጠህ እኔ የማውቀው ክብር አለህና ስለዚህ ነው፡፡ ይልቁንስ እንዳልኩህ በተቀበርኩበት ቦታ እንድትቀበርልኝ ቃልኪዳን ግባልኝ›› ብለው ማለዷቸው፡፡ ይህንንም ሲባባሉ እንዲህ የሚል ቃል መጣላቸው፡- ‹‹ከወዳጄ ከሀብተ ማርያም አንደበት ይህ ቃልኪዳን አይወጣም፣ ዳግመኛም ወዳጄ ተክለ ሃይማኖት ሆይ! እርሱ በወደደው የሚቀበር አይደለምና እኔ ከተቀበርኩበት እንድትቀበር ብለህ የምታስገድደው ለምንድን ነው? እኔ በወደድሁት ቦታ ይቀበራል እንጂ›› የሚል ቃል ተነገረ፡፡ አቡነ ተክለሃይማኖትም እየለመኑናና እየሰገዱ ከሥላሴ ዙፋን ፊት ተንበረከኩ፡፡ ሦስተኛውም ‹‹ይሁን እንዳልከው ይቀበርልህ›› የሚል ቃል ተሰማ፡፡ ዳግመኛም ‹‹በአንተም አጽም በሀብተ ማርያምም አጽም ቦታህ ከመቅሰፍታት ትዳንልህ፤ ልጆችህ ግን በቸነፈር ደዌ ቢሞቱ ከሰማዕትነት ተቆጥሮላቸው ወደ መንግሥተ ሰማያት እንዲገቡ በራሴ ምዬ ቃልኪዳን ገብቼልሃለሁ›› አላቸው፡፡ በዚህም ጊዜ አቡነ ተክለሃይማኖት እጅግ ደስ ተሰኝተው ሦስት ጊዜ ሰገዱ፡፡

➯ከዚህም በኋላ መልአኩ ለአቡነ ሀብተ ማርያም ክብሯ እንደ ጽርሐ አርያም የሆነች አገርን አሳያቸው፡፡ ሥፍር ቁጥር የሌላቸውም ቅዱሳን መላእክት በውስጧ ተድላ ደስታ ያደርጉባት ነበር፡፡ አባታችንም መልአኩን ‹‹ይህች ክብሯ ፍጹም የሆነችን አገር ማን ትባላለች በውስጧ ለመኖር በእጅጉ ወድጃለሁና›› ብለው ሲጠይቁት መልአኩም ‹‹ይህችማ አገር የአባትህ የተክለ ሃይማኖት አጽም ያረፈባት ደብረ ሊባኖስ ናት፤ ከእርሱም ጋር በክብር እስክትነሣ ድረስ በውስጧ ትቀበርባት ዘንድ ለአንተም ተሰጥታሃለችና ደስ ይበልህ፡፡ አባትህም እንደ ኢየሩሳሌም እንደትሆንለት ቃልኪዳን ተቀብሎባታል›› አላቸው፡፡......
September 1, 2026 48