ህወሓት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ በፌደራል መንግስት ይሁንታ የሚንቀሳቀሱ በመሆናቸው ለአሸማጋይነት ብቁ አይደሉም አለ‼️
የትግራይ ክልል መንግስትን በኃይል የተቆጣጠረው እና በምርጫ ቦርድ ህጋዊ እውቅናውን የተነፈገው ህወሓት፤ ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ ከፌደራል መንግስት ቀጥተኛ ትዕዛዝ የሚቀበሉ፣ ግልፅ የሆነ የሰላም አጀንዳ እንዲሁም የሰላም ሃሳብ ሳይዙ የሚንቀሳቀሱ፣ የዓለም አቀፍ አሸማጋይነት ዋና መመሪያ የሆኑትን ነጻ እና ገለልተኝነት፣ ተከታታይነት ያለው ጥረት የማያደርጉ እና ይህን መስፈርት የማያሟሉ መሆናቸውን በመጥቀስ ለአሸማጋይነት ብቁ እንዳልሆኑ አስታወቀ።
ድርጀቱ፤ ኦባሳንጆ በፌደራል መንግስት ስር እንደወደቁ በመጠቆም ለሌላ አሸማጋይ በሩ ክፍት እንደሆነ አስታውቋል።
በትናንትናው ዕለት ማምሻውን ባወጣው ይፋዊ መግለጫ፤ የአፍሪካ ኅብረት የቀንዱ ልዩ መልዕክተኛ እና የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ጋር በተያያዘ ያለውን ጠንካራ ቅሬታ አንስቶ፣ የሰላም ሂደቱ ነፃ እና ገለልተኛ አሸማጋይ እንደሚያስፈልገው አጽዕኖት ሰጥቷል።
ህወሓት ከጦርነቱ በፊት የነበረውን የክልሉ ምክር ቤት ወደ ስራ ከመለሰ በኋላ ጊዜያዊ አስተዳደር የሚለውን መጠሪያ ማቆሙ የሚታወስ ሲሆን ከጥቂት ሳምንታት በፊት ኦባሳንጆ መቀለ ሲገቡ ከፌደራል መንግስቱ ጋር እየሰሩ ያሉት የቀድሞው የፓርቲው አመራሮች ይሁንታን ችረውት ነበር።
ሕወሓት እና የፌዴራላዊ መንግሥቱ የፕሪቶሪያን ስምምነት ከተፈረመ ከጥቂት ወራት በኋላ አራት ዓመት ሊያስቆጥር መሆኑን ያስታወሰው ህወሓት፤ የስምምነቱ ትግበራ በአፍሪካ ኅብረት ከፍተኛ የልዑካን ቡድን እና በዓለም አቀፍ አጋሮች ችላ ተብሏል ያለ ሲሆን የስምምነቱ ዕድል በፌዴራል መንግሥቱ ውሳኔ ስር ወድቋል ብሏል።
በተጨማሪም የፌዴራል መንግሥቱ ስምምነቱን ከመፈጸም ይልቅ ክልሉን በኢኮኖሚ እና ከበባ በማድረግ ከፍተኛ ወድመት አየፈፀመት ነው ሲል ወንጅሏል፡፡
ህወሓት፤ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን፣ ወታደራዊ ከበባን፣ የሥነ-ልቦና ጦርነትን እና ያልተቋረጠ የድሮን ቅኝትን አጠናክሮ ቀጥሏል ሲል ፌደራል መንግስቱን ወቅሷል።
በተጨማሪም ከወር በፊት የተከሰተውን ግጭት በማንሳት ህወሓት “በምዕራብ ትግራይ” በሚገኘው ሸረሪና በተባለ ቦታ በትግራይ ጸጥታ ኃይሎች ላይ ጥቃት በመሰንዘር እና በልዩ ልዩ አካባቢዎች የድሮን ጥቃቶችን በመፈጸም የተኩስ ማቆም ስምምነቱን በተደጋጋሚ ጥሷል ብሏል።
አክሎም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን (ዶ/ር)ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አደረጉት ባለው ንግግር የስምምነቱን ይዘት ሙሉ በሙሉ መረሳቱን “ሁሉም ነገር ተርስቷል” ማለታቸውን የጠቀሰ ሲሆን፣ ስምምነቱ የተፈረመው በተቋማት ሳይሆን “በሦስት ግለሰቦች” መሆኑን በመግለጽ ስምምነቱ ህያው እንዳልሆነ አሳይተዋል፣ በማለት ወንጅሏቸዋል።
ኦባሳንጆን በተመለከተ ደግሞ በተናጠልና በነፃነት ከመንቀሳቀስ ይልቅ በፌዴራል መንግሥቱ ፍላጎት እየተመሩ እንደሆነ ገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ኦባሳንጆ በናይጄሪያ የቢያፍራ የእርስ በእርስ ጦርነት የታየውን ሂደት እንደ የሰላም ሞዴል ማቅረባቸውን አግባብ አይደለም ብሏል። ይህን አሉ ያለው ደግሞ የምክክር ጉባኤ መክፈቻ ላይ ነው።
ህወሓት የቢያፍራ ታሪክ ወታደራዊ ከበባን፣ የኢኮኖሚ እገዳን፣ ረሃብን፣ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሰ አስከፊ መከራን እና በኃይል የተጫነ ውልን የሚያስታውስ እንጂ በተደራዳሪዎች መካከል የተደረገ የሰላም ስምምነት አይደለም ሲል ገልጾታል።
ኦባሳንጆ በሰኔ ወር ወደ ትግራይ መጥተው ውይይት ካደረጉ በኋላ በሁለት ሳምንታት ውስጥ እንደሚመለሱ ቃል ገብተው ነበር ያለው ድርጅቱ፣ የፌዴራል መንግሥቱ “የሀገራዊ የምክክር መድረክ” እስከሚያጠናቅቅ ድረስ እንዲጠብቁ ባዘዛቸው መሠረት ጉዟቸውን ሳያሳውቁ ለሁለት ወራት ያህል ዘግይተዋል፤ ይህም ለማደራደር ሳይሆን ቀጥተኛ የመንግስትን ትዕዛዝ ተቀብለው የሚንቀሳቀሱ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው ብሏል።
ህወሓት ኦባሳንጆ ወደ ትግራይ በተመለሱበት ሰዓት ያለ ምንም ቅድመ ማሳወቅ እንዲሁም ጭብጥ ሳይዙ ነው እንደመጡ አስታውቋል።
በተጨማሪም ያለ ተጨባጭ የሰላም ሀሳብ እና ግልጽ የሆነ አጀንዳ ሳይዙ በመምጣታቸው ለሰላም ሂደቱ ያመጡት አዎንታዊ ለውጥ የለም ብሏል።
የዓለም አቀፍ አሸማጋይነት ዋና መመሪያ ገለልተኝነት፣ ነፃነት እና ተከታታይነት ያለው ጥረት መሆኑን ያስታወሰው መግለጫው፤ ኦባሳንጆ እነዚህን መሠረታዊ ባህሪያት ሳያሟሉ ቀርተዋል የሚል ድምዳሜ ላይ መድረሱን በማሳወቅ ክልሉ አሁንም ቢሆን ለአስተማማኝ፣ ፍትሐዊና በጊዜ ገደብ የተደገፈ የሰላም ውይይት ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።

21
7
5September 7, 2026 5K 3 1