ሩፋኤል - የአማራ እና ኦሮሞ ሕዝቦች የአብሮነት ምስክር በዓባይ ወንዝ! ጳጉሜን 3 በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ… — Sheger Press️️ — TG.ME

Sheger Press️️Photo
ሩፋኤል - የአማራ እና ኦሮሞ ሕዝቦች የአብሮነት ምስክር በዓባይ ወንዝ!

ጳጉሜን 3 በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ተከታዮች ዘንድ የሩፋኤል መንፈሳዊ በዓል የሚከበርበት ቀን ነው፡፡ በሁሉም አካባቢ የሚከበር በዓል ቢኾንም በደጀን እና ጎሐጽዮን መካከል በዓባይ ወንዝ ሁለቱ ዳርቻዎች ላይ የሚከናወነው አከባበር ግን በድምቀቱ፣ በአከባበር ሥነ- ሥርዓቱ እና በተሳታፊዎች ቁጥር ልዩ እንደኾነ ይነገርለታል።

በአማራ እና በኦሮሞ ማኅበረሰብ ዘንድ ለረጅም ዓመታት በአብሮነት ሲከበር የቆየው ይህ የጋራ ሃይማኖታዊ በዓል ጊዜ በማይሽረው ፍቅር እና ትስስር ዘንድሮም እየተከበረ ነው። ዓባይ ላይ የሚከበረው የሩፋኤል በዓል ሃይማኖታዊ ክዋኔ የሚከናወንበት ብቻ አይደለም። የሁለቱ ታላላቅ ሕዝቦች የደም፣ የባሕል እና የጽኑ ወንድማማችነት ትስስር ማረጋገጫም ጭምር እንጂ።

አሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ያነጋገራቸው በደጀን አቅጣጫ በሚገኘው ዓባይ በረሃ ውስጥ ኩራር ቀበሌ ነዋሪ የኾኑት እሱባለው አባተ ይህንኑ ሀሳብ የሚያጠናክር መልዕክት ነግረውናል። ዓባይ ወንዝ ላይ በሚከበረው የሩፋኤል በዓል ልዩ ትዝታ እንዳላቸውም አጫውተውናል።

ወደ ኋላ በትዝታ ተጉዘው ከ1970 እና 80ዎቹ ዓ.ም ወዲህ ያለውን የበዓሉን አከባበርም ገልጸውልናል። በዚህም ጳጉሜን 3 ዓባይ ወንዝ ላይ ለሚከበረው የሩፋኤል በዓል ከአማራ እና ኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የሚሠባሠቡ የበዓሉ ተሳታፊዎች በበዓሉ ዋዜማ ቀድመው እንደሚገኙ ነግረውናል። በዓባይ ወንዝ ዳርቻ ላይም ጊዜያዊ መጠለያ አዘጋጅተው እንደሚያድሩ ነው የገለጹልን።

የሚያድሩትም ከአማራ ክልል የተጓዙት የዓባይን ድልድይ ተሻግረው በኦሮሚያ ክልል አቅጣጫ በቀኝ በኩል፣ ከኦሮሚያ ክልል የተጓዙት ደግሞ ድልድዩን ተሻግረው በአማራ ክልል አቅጣጫ በቀኝ በኩል ባለ የወንዙ ዳርቻ እንደኾነ ነው የነገሩን። ይህም የሚኾነው የዘመን ሽግግርን ለመግለጽ ነው ብለውናል። በቀኝ በኩል የመኾናቸው እሳቤ ጥሩ ነገር የመመኘት እና ብሩህ ነገር ይመጣል ብሎ የማሰብ መኾኑን ጠቅሰውልናል።

የኩራር ነዋሪ የኾኑት እሱባለው አባተ በበዓሉ ቀንም ባደሩበት አቅጣጫ በሃይማኖት አባቶች የተባረከውን ጸበል ተጠምቀው፤ የሩፋኤልን የንግሥ ሥርዓት በአንድነት ተገናኝተው በሩፋኤል ቤተክርስቲያን ያከብራሉ። የንግሥ ሥርዓቱ እንዳበቃም የውኃ ዋና ችሎታ ያላቸው የሁለቱም አካባቢ የበዓሉ ታዳሚዎች በጋራ ዓባይ ወንዝ ላይ ይዋኛሉ። የዋና ውድድርም እንደሚያደርጉ ገልጸውልናል። ቀሪ የበዓሉ ተሳታፊዎች ደግሞ በድልድዩ እና በዓባይ ወንዝ ዳርቻ ላይ ኾነው በጋራ ዋናተኞቹን ይመለከታሉ። ጠንካራ ዋናተኞቹንም እንደሚያበረታቱ ነው የነገሩን።

ሳቅ እና ጨዋታው ይደራል፤ በጋራ ይዘምራሉ። ስለክራሞታቸው፣ ስለጤናቸው፣ ስለቀያቸው ሰላም፣ ስለሀገር ሰላም እና ስሌሎቹ ጉዳዮች በጠለቀ ቤተሰባዊ ስሜት ይጠያየቃሉ። በጋራ ማዕድ ይጋራሉ። የተለያዩ ባሕላዊ ቁሳቁሶችን ይገበያያሉ። አብሮነትን የሚያሳዩ ክዋኔዎች ሁሉ ሲከናወኑ ይውላሉ። ከዛም ፈጣሪ ለቀጣዩ ዓመት በሰላም እንዲያገናኛቸው ተመኝተው ይሠነባበታሉ።

በዚህ የእርስ በርስ ግንኙነት ብዙ ወዳጆች ማፍራታቸውን እና አንዳቸው በአንዳቸው ደስታ እና ሀዘን እንደማይለያዩ ጠቅሰውልናል። የእራሳቸው የቅርብ ዘመዶች እስከ አምቦ ድረስ በጋብቻ መተሳሰራቸውንም ነግረውናል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በጸጥታ ሁኔታው የበዓሉ ተሳታፊ እየቀነሰ መምጣቱን አንስተውልናል። የበዓሉ ተሳታፊ የመቀነስ ሁኔታ ቢኖርም ዘንድሮም በዓሉ ነባር እሴቱን ጠብቆ እየተከበረ እንደሚገኝ ገልጸውልናል።

የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪ ማኅበረሰቦች በአንድነት እና በፍቅር የሚያከብሩበትን ይህን ሃይማኖታዊ መሠረት ያለው ትልቅ የአብሮነት እሴት ወደፊት ማጠናከር እንደሚገባም መክረዋል። ለዚህም ከሃይማኖት አባቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከምሁራን፣ እና ከራሱ ከሕዝቡ ትልቅ ሥራ ይጠበቃል ብለዋል።

የምሥራቅ ጎጃም ዞን ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ የቅርሰ ጥበቃ እና እንክብካቤ ቡድን መሪ ሙሉዓለም አየሁ ዓባይ ወንዝ ላይ የሚከበረው የሩፋኤል በዓል ከቱሪዝም ዘርፍ አኳያ በርካታ የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች የሚሳተፉበት እንደኾነ ነግረውናል። ጠቃሚነቱን ለማጉላትም የማስተዋወቅ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ ነው የገለጹልን። በቂ ግን አይደለም ብለዋል።

አብሮነትን ለሚያጎለብተው ለዚህ የቱሪዝም መዳረሻ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት እና የጎብኝዎች ማረፊያ ያስፈልጋል ነው ያሉት። በቀጣይ በማኅበረሰቡ ትብብር፤ በመንግሥት ድጋፍ እና ልማት ላይ በሚሠሩ ባለሃብቶች ይህ አካባቢ እንዲለማ እና ለቱሪዝም ዘርፉ የጎላ አስተዋጽኦ እንዲኖረው በርካታ ሥራዎች መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል።

#አሚኮ #VisitAmhara #ኢትዮጵያ🇪🇹

#ባሕር_ዳር #ጳጉሜን_03_2018_ዓ_ም

✍️ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
❤25🙏4
September 8, 2026 3K 8 5