#ዐካኪ እና #ዘራፍ
#ዐካኪ_ዘራፍ ዕድሜ ልኬን የሰማኹት ሐረግ ነው። በልጅነት “ዘራፍ፣ አቃቂ ዘራፍ” ሁሉ እንል ነበር - ከዐካኪ ይልቅ አቃቂ ለቂርቆሶች (ለጆሯችንም) ቅርብ ስለነበር። እንደው ዘራፍዬ፣ ዘራፍ ዘራፍዋ … አብሬ ዘፍኛለኹ፤ በፉጨትም ቢኾን።
“ዐካኪ ምንድነው? ዘራፍስ?” ብዬ ጠይቄ ግን አላውቅም፤ ትርጉሙን የማላውቀው መስሎኝ አያውቅም።
ትናንት አንድ መዝገበ ቃላት #ኤዲት እያደረግኹ አንድ አተረጓጎም አልጥም ብሎኝ፣ አማራጭ ፍለጋ የአለቃ #ደስታ_ተክለ_ወልድን መዝገበ ቃላት እያገላበጥኩ ነበር። ከቃል ቃል እየተሻገርኹ፣ “ዐካኪ” ጋ ደረስኹ። ፍችው አስገረመኝ፦
“#ዐካኪ፤ (ሐካኪ)፤ ያከከ፣ የሚያክ፤ ቧጫሪ፣ ቧጣጭ፣ ሰንዛሪ፣ ጥፍራም አውሬ።”
እና “ዐካኪ ዘራፍ”ን ከቧጫሪ፣ ቧጣጭ፣ ሰንዛሪ፣ ጥፍራም አውሬ ጋራ ምን አገናኘው?
“ዐካኪ ዘራፍ፤ የፉከራ ቃል፤ ዐካኪን የሚዘርፍ፣ የሚቀማ፣ ካንበሳ፣ ከድብ በግን የሚያስጥል (1ኛ ሳሙ. 17፥34-37)። ዐካኪ ‘አካኪ’ ተብሎ ቢጻፍ ግን፦ አዋኪ፣ አሸባሪ፣ በጦር ሜዳ ተከራካሪ፣ የጎበዝ ጎበዝ ማለት ነው (1ኛ ሳሙ. 17፥46-51-37)።
(መጀመሪያ በተጠቀሰው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል፣ የተናቀው ብላቴና ዳዊት በጎቹን ከአንበሳ እና ከድብ መንጋጋ ስለመንጠቁ ለሳኦል ይነግረዋል - አለቃ ደስታ ይህን ይዘው ዳዊት “ጥፍራም አውሬን የነጠቅኹ ዐካኪ ዘራፍ ነኝ” እንዳለ ይተረጉሙልናል።)
የ#ከሳቴ_ብርሃን_ተሰማ መዝገበ ቃላት ደግሞ “አካኪ ዘራፍ”ን ሲፈታው እንዲህ ይላል፦
“በጥኑ ጦርነትና ባፍላ ውጊያ ላይ ዐምስት ወይም ዐሥር የኾኑ የተወረወሩ የጠላቶች ጦሮች ጋሻውን ወይም ሰውነቱን ሳይወጉት አምልጦ እነዚያ ተወርውረው የሳቱትን ጦሮች የዘረፈ አካኪ ዘራፍ ነው ይባላል።”
(ኹለተኛው የአለቃ ደስታ ጥቅስ ከዚህ ጋር ይስማማል፤ ዳዊት ጎልያድን በወንጭፍ ገድሎ፣ በጉልቤው ጎልያድ ሰይፍ አንገቱን ቆርጦ ይጥላል፤ ሰይፉን ዘርፎ ይሰይፈዋል፡፡ - ዳዊት እዚህም አ(ዐ)ካኪ ዘራፍ ኾኖ ይገኛል) -- [This is what we call #intertextuality in literature.]
ለማንኛውም “ዐካኪ ዘራፍ” - የገዛ በጎቹን ከነጣቂ መንጋጋ የሚያድን ወይም የተሰነዘረበትን የጠላቱን/የተጻራሪውን መሣሪያ ጠላቱን ለማጥቃት የሚጠቀም ነው።
ዝም ብሎ ፉከራ ወለድ፣ የስሜት ሐረግ እንዳይመስላችኹ።
የጦር ቃል ብቻም እንዳይመስላችኹ።
ራሳቸውን/ ምንትነታቸውን (identity)/ እሴቶቻቸውን (values)/ ልጆቻቸውን ከነጣቂ የዘመን መንጋጋ ራሱ ዘመኑ በወለደው መላ የሚያድኑትን ብርቱዎች ኹሉ ለማሞገስ የሚኾንም ቅፅል ነው።
አቃቂ ዘራፍ ግን አይባልም። 😉
© ቴዎድሮስ አጥላው
ሁሌም ማንበብ!
10
9
4
1August 18, 2026 3.7K 12