የማይሸለምበት 'ሪሲሊንግ🥊 ""ለምንድነው ድንገት የተውከኝ?" አለችኝ፤ "እኔ'ንጃ ምን አልባት ፈርቼሽ… — መጽሐፍቶችን በpdf📚 — TG.ME

🥇የማይሸለምበት 'ሪሲሊንግ🥊

""ለምንድነው ድንገት የተውከኝ?" አለችኝ፤

"እኔ'ንጃ ምን አልባት ፈርቼሽ ይኾናል!"
በዐይኗ እየተቅለሰለሰች "ም'ኔ አስፈራህ? 'ትባ'ላለች' አሉህ?"

ጥቁረቷ፥ የዐይኗን ውበት አጉልቶታል፤
ጥቁረቷ፥ 'ጥርሰ በረዶ' እንድትባል ያደረጋት ይመስለኛል።

ስታምር!

ትክ ብዬ ዐያየኋት፤
"የመወደድ ረኀብ ያለብሽ ይመስላል" አልኳት።

ምን ማለት ነው??

"የሚወደኝ ዐጥቼ ማለት ነው?" ሳቀች፤ አሳሳቋ ፌዝ አዝሏል።
"አይምሰልሽ! የአንዳንድ ረኀብ ምንጭ እኮ፥ የአቅርቦት ዕጥረት አይደለም፤ የአስተዳደግ ጠባሳም ሊኾን ይችላል።

"ቀጠሮ ኖርበት፥ የክት ልብሱን አጥቦ ፀሐይን እንደሚጠብቅ ሰው ነው፥ ቀልብሽ፣ ቆሌሽ... ሁሉ ነገርሽ መወደድሽን የሚጠብቀው ....

"እመኚኝ ቲጂ

"ማስከተል ለምደሻል ...ፍላጎት አምጠሽ፣ አስወልደሽ፣ አሳድገሽ እንዳላወቀ፥ ድንግጥ ብለሽ 'እንዴት እንደዚህ ሊሰማ ቻለ!?' ብለሽ መካድ ለምደሻል !

ለመወደድ ምቹ ኾኖ፥ ጠዋት ማታ ከለፉ በኃላ 'በዚህ መንገድ አላሰብኩም' ብለው ከሚያለግጡት ውስጥ ነሽ።
ከልብ ያልሆነ ፈገግታ ፊቷ ላይ ብርት ብሎ ጠፋ፤

"ያንተ ጠላት አንተ ነህ። መታገስ ሲያቅትህ ለመሸሽ የሰጠኸው ሰበብ ነው! ግርማ፥ እመነኝ የማጣት ፍርሃት አለብህ ...."

"አይ ቲጂ...

"እኔ የማቃጥለው ትርፍ ግዜ የለኝም!
የመታኝን ዐይነት እንቅፋት እንዳየሁት ነው የማውቀው፤ ከነ ሕመሙ ነው የማስታውሰው!

"እኔ የሰው trauma የማከም ዐቅም ላይ አይደለሁም ...!
"አሁን ባላሁበት ኹኔታ አልችልሽም።
"ያሸሸኝ የዐቅም ጉዳይ ነው!... መንገድሽን ዞ'ር ብለሽ ዕይው፤ ሲርቁሽ የምትከተይው እና ሲቀርቡሽ የምትርቂው ርቀት ተመሳሳይ ይመስለኛል!

"ፈራሁሽ !!

"እንዳንቺ ዐይነት ሰዎች እንደተወደዱ ካረጋገጡ በኋላ፥ ቀስስ ብለው ከ'ሪትሙ' ይወጣሉ፤ ለመወደድ ያደረጉት የከፈቱትን ሁሉ፥ ዝግትግት ያደርጋሉ ...

"...'Look'...

መጀመርያ ሰሞን የምትኾኚልኝ ነገር ሁሉ እንደእጮኛሽ ነበር፤ የመጀመርያ ሰሞን የምታወሪበት ድምፀት እንኳን የለም! እንክብካቤሽ፣ መንገድ ስንሄድ ሽጉጥ የምትይብኝ፣ መውድድሽ በየምክንያቱ፣ ማክበርሽን በየሰበቡ የምታሳይኝ ነገር ሁሉ ራሱን አጥፍቷል።

"የመንገደኛን ኮቴ፥ መከተል አልችልም! ትኩረቴን የሚሻ ሕልም አለኝ፤ የኔን ግዜ የሚፈልግ ሌላ ትግል አለኝ!

"በኔ አታሳ'ብ ግርምሽ፤ ቶሎ መወደድ ለምደህ ነው! ሳትጠይቅ ማግኘት አበላሽቶህ ነው!!

"ሳትበረታ ላ'ጣኸው ሁሉ፥ ያንተ ጥፋት እንዳልኾነ ለጭንቅላትህ መንገር ለምደህ ነው። ድክመቱን ሁሉ የሰው ችግር አድርጎ እንደሚተነትን ሰው፥ የሚያሳዝነኝ የለም።"

"ቲጂዬ! እውነትሽን ነው፤ ዐቅም ስለሌለኝ ነው የሸሸሁት።

"... 'ከማልችለው ጋር ምን አታገለኝ ብዬ ነው! አንቺ ደሞ ኹኔታሽ ሁሉ እንደወፍ ነው፤ ሲከተሉሽ ትበር'ያለሽ፤ ስረጋጋ፣ ስቆም መጥተሽ፥ አናቴ ላይ ትወጫለሽ!

ደስታ ሊያስደንሰኝ ሲጀምር ትበር'ያለሽ ...
እንደቅድሙ አልሳቀችም ....

"ዳንስ መቼ ትችል እና ...ይልቅ ግርምሽ 'ሪስክ' የማይወስድ ሰው አልወድም፣ የተበላሸ ነገር ለመሥራት የማያቅድ ወንድ፣ የተሠራ ነገር የሚያሳድድ ሰው፥ ያሳዝነኛል! በተለይ ወንድ..."

"ካንቺ ባ'ላቅም ....!

"ጀግና የሚያተርፈውን ሳያሰላ አይታገልም። ጀግና ኹኔታን እና ዋጋን አስልቶም ይሸሻል፤ እስከማውቀው... ዐለም ላይ፥ የመወደድ ረኀብ ካለበት ሰው ጋር 'እንደተጣበሰ' ፣ እንደተጋባ የሚያሳዝነኝ የለም!...

"ጠዋት ማታ ሥራ አለበት። ማባበል አለበት፤ ውድድር አለበት፤ ኑሮው ሁሉ 'ሪሲሊንግ' በይው... ዋንጫ፣ ሜዳልያ፣ የማይሸለምበት 'ሪሲሊንግ'!

"ማንም እንዲህ ብሎኝ፣ የትኛውም ወንድ አንተ ባልከው መንገድ ተረድቶኝ አያውቅም !"

"ይኾናል... እኔ ግን 'አንተ ብቻ ነህ፥ ያመለጥከኝ!' እንዳልሺኝ ነው የምቆጥረው !!"

© Adhanom Mitiku

ሁሌም ማንበብ!
👍14❤8
August 28, 2026 1.5K 8