በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የ8ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል 97 ነጥብ 4 በመቶው ወደ ቀጣይ ክፍል ተሸጋግረዋል-ምክትል ርዕሠ መስተዳድር አንተነህ ፈቃዱ
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የ2018 የትምህርት ዘመን የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ውጤት ይፋ ሆኗል።
የክልሉ ምክትል ርዕሠ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ ውጤቱን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።
ምክትል ርዕሠ መስተዳድሩ በመግለጫቸው እንደገለጹት በ2018 ዓ.ም ለ8ኛ ክልል አቀፍ ፈተና ከተመዘገቡት ውስጥ 85,531 ተማሪዎች በፈተናው ተቀምጠዋል።
በዘንድሮው ዓመት የማለፊያ መቁረጫ ነጥብ ለመደበኛ ተማሪዎች 50% እና ከዚያ በላይ፣ ለአካል ጉዳተኞች ደግሞ 45% እና ከዚያ በላይ እንዲሆን መወሰኑን ተናግረዋል።
በዚህም መሠረት፦ 83,342 ተማሪዎች ማለትም 97.4 በመቶ የማለፊያ ነጥብና ከዚያ በላይ አስመዝግበው ማለፍ መቻላቸውን አመላክተዋል።
የዘንድሮ ዓመት ውጤት ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር የማለፍ ምጣኔው 61.5% ዕድገት አሳይቷል ነው ያሉት።
በትምህርት ቤቶች እና በትምህርት ዓይነቶች ከፍተኛ ለውጥ መመዝገቡን ምክትል ርዕሠ መስተዳድሩ ገልጸዋል።
በአጠቃላይ ከነበሩት 1 ሺህ 538 አስፈታኝ ትምህርት ቤቶች መካከል 1 ሺህ 17 ወይም 66.1 በመቶ የሚሆኑት ተማሪዎቻቸውን ሙሉ ለሙሉ ማሳለፋቸውን ተናግረዋል።
ይህም በ2017 ዓ.ም ከነበረበት 268 ወይም 17.6 በመቶ ትምህርት ቤቶች አንጻር ከ200% በላይ ጭማሪ ማሳየቱን ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል በ2017 ዓ.ም 56 ትምህርት ቤቶች ምንም ተማሪ ያላሳለፉ የነበረ ሲሆን፣ በ2018 ዓ.ም ግን አንድም ተማሪ ያላሳለፈ ትምህርት ቤት የለም ብለዋል።
በአብዛኞቹ የትምህርት ዓይነቶች ላይ ከፍተኛ የውጤት ጭማሪ የታየ ሲሆን፣ በተለይም በሒሳብ፣ በእንግሊዝኛ እና በዜግነት ትምህርት ላይ ዕድገት መታየቱን ገልጸዋል።
በአንጻሩ በከምባቲኛ እና በሊቢቲሶ የትምህርት ዓይነቶች ላይ መጠነኛ የውጤት መቀነስ ተመዝግቧል።
ኩረጃን ለማስቀረት ጠንካራ የፈተና አስተዳደር ስርዓት መዘርጋቱን የገለፁት ምክትል ርዕሠ መስተዳድሩ በተለይም ፈተና በክላስተር ማዕከላት ክልላዊ ሱፐርቫይዘሮች ጭምር ተመድበው እንዲሰጥ መደረጉን አብራርተዋል። ኩረጃን የሚጸየፍ ትውልድና ማህበረሰብ ለመፍጠር የተደረጉ ጥረቶች ውጤታማ እንደነበሩ አንስተዋል።
ዘንድሮ የተመዘገበው ውጤት የመጣው ቢሮው በተከታታይ ዓመት ለትምህርት ጥራትና ለተማሪዎች ውጤት መሻሻል ሳይንሳዊ መሆኑ መልኩ የትኩረት መስኮችን ለይቶ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ የተገበራቸው ስራዎች ውጤት መሆኑንም አመላክተዋል።
ተማሪዎችን ለፈተና የማዘጋጀት ስራ በከፍተኛ ሁኔታ መሰራቱንም ገልጸው፥ በተለይም የማጠናከሪያ ትምህርት፣ ሞዴል ፈተና እና የስነ-ልቦና ግንባታ እንደተሰጣቸው። በዚህም በዘንድሮ ዓመት ከዚህ ቀደም በተለየ መልኩ በመዋቅሮች መካከል ተቀራራቢ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።
የተማሪዎች፣ የመምህራን እና የተማሪ ወላጆች የነበራቸው ቁርጠኝነት ለተመዘገበው ወጤት ከፍተኛው ድርሻ እንደሚወስዱ ምክትል ርዕሠ መስተዳድሩ ተናግረዋል።
ከክልሉ ርዕሠ መስተዳድር ጀምሮ የክልሉ የመንግሥት ዋና ተጠሪ፣ የቢሮ ማኔጅመንት፣ የሆሳዕና ትምህርት ኮሌጅ እና በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደነበር አውስተው ለዚህም ላቅ ያለ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በይዲድያ ተስፋሁን
ስለ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት ከታች ያሉ ገፆቻችንን ይጎብኙ
ዌብ ሳይት፥ https://www.cerboed.gov.et/
ቴሌግራም፦ https://t.me/cer_eb
ቲክቶክ፥ https://[email protected]_t=8mbyN9TPpyA&_r=1
ኢንስታግራም https://www.instagram.com/cers_education_bureau?igsh=M25rY2J5ZWlxaHd1&utm_source=qr
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/profile.phpid=61552584825405&mibextid=kFxxJD
ዘውትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Telegram
Central Ethiopia Regional State EDUCATION BUREAU
Regional Education Bureau

16
4July 20, 2026 9.3K 6