ሀሳቤ መች አስቦልኝ ፣ እዚህ አድርሶኝ ማወቄ
መች ቁጥር ይገባና ፣ ድል ያረኩት ተጠንቅቄ
ከንቱ መሆኑ ጭንቀቴ ፣ ማወቁ መቼ ተሳነኝ
ሰውነት ቢይዘኝ እንጂ
ከእምነቴ ሀይል በላይ ፣ ገሀድ ህይወቴ ቢጫነኝ ።
"ያልፋል" አትብለኝ አልፋለሁ
ልክ ነው ይረሳል ረግፋለሁ
እውቀቴ አድማስ ፣ቢሻገር ብሰማም ሲባል ብዙ
ሰማይ ከመሬት ሲላቀቅ ፣ ይጀምረኛል መቅበዝበዙ።
"ያልፋል "ማለት አያለፋም
ትናንትና ምን ቢዘምም ፣ ከዛሬ ጽልመት አይከፋም
ልክነትህን ልቀበል ፣ ካለመቻሌ ተስማማ
ድንግዝግዝታዬ ይዋጥልህ ፣ ዳግም ተስፋን እንድጫማ ።
ሀሳብን ሽቼ አይደለም ፣ ምክርን ውስጤ ናፍቆ
የሚናገርን አንደበት ፣ ምክንያት ከውጤት አራቆ
"ከብደኝ ፣ደከመኝ" ስልህ ፣" ለምን ?" እንዳይሆን መልስህ
ይልቅ ዝም በልና ፣ አጥር ሁንልኝ በክንድህ።
ሳትደርስብኝ ልትደርስልኝ አትታገል
መች ተችሎት ፣ ተግሳጽ ሁሉን መገላገል ።
" ከበደኝ ፣ ደከመኝ " ስልህ ፣ "እንዴት?" እንዳይሆን ምላሽህ
ትከሻዬ እና ቀንበሬን ፣ አታወዳድረው ከራስህ
ባለፋከው ነገር ሚዛን ፣ አይነውረብህ ሽንፈቴ
የእኔ አቅም እዚህ ድረስ ነው ፣ "ልክ ነሽ " በለኝ በሞቴ ።
ምሕረት ዘነበ
5
2
1August 1, 2026 132