“ካቀድነው በላይ ለመፈጸም ሌት ተቀን መስራት ይጠበቅብናል”
- ወ/ሮ ዓይናለም ንጉሴ (የገቢዎች ሚኒስትር)
ሐምሌ 21/2018 ዓ.ም (የገቢዎች ሚኒስቴር)
በቢሾፍቱ ከተማ ሲካሄድ የቆየው የገቢዎች ሚኒስቴር እና የጉምሩክ ኮሚሽን የ2018 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2019 በጀት ዓመት እቅድ ውይይት መድረክ በዛሬው እለት ተጠናቋል።
የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ መድረኩን ባጠቃለሉበት ወቅት የ2018 በጀት ዓመት የሁለቱም ተቋማት እቅድ አፈጻጸም እጅግ ውጤታማ ሆኖ መጠናቀቁን በድጋሚ አስታውሰዋል፡፡
በውይይት መድረኩ ብዙ ጠቃሚ እና ለወደፊቱ እንደግብዓት የሚወሰዱ ሀሳቦች መነሳታቸውን የጠቆሙት ሚኒስትሯ በውይይቱ ልክ ለመተግበር ሌት ተቀን መትጋት ይጠበቅብናል ሲሉ አሳስበዋል፡፡ የ2019 በጀት ዓመት አፈጻጸምም ከአቀድነው በላይ የሚሳካበት እና አስደሳች ውጤት የሚመዘገብበት እንደሚሆንም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
የጉምሩክ ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ (ዶ/ር) በበኩላቸው አሁን ያለውን እና ቀጣይ ተልዕኮዎችን መሸከም የሚችል መዋቅር እና ብቃትን መሰረት ያደረገ የሰው ኃይል ስምሪት በተያዘው የበጀት ዓመት ተግባራዊ ከሚደረጉ ቁልፍ ጉዳዮች መካከል አንዱ መሆኑን አብራርተዋል።
በዘንድሮው የበጀት ዓመት በገቢ አሰባሰብ አዲስ ታሪክ የሚጻፍበት እንደሆነ የተናገሩት ኮሚሽነሩ ለገቢ አሰባሰቡ ስኬት ተግዳሮት የሚሆኑ ጉዳዮች ከወዲሁ ተለይተው የመፍትሔ አቅጣጫዎች መቀመጣቸውን ገልጸዋል።
በመድረኩ የገቢዎች ሚኒስቴር የ2018 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸምን እና የ2019 በጀት ዓመት እቅድ በሚኒስቴሩ የስትቴጂክ ፕላን እና ፕሮጀክት አስተዳደር ዳይሬክተር በአቶ ተመስገን ተሰማ እንዲሁም የጉምሩክ ኮሚሽን የ2018 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸምን እና የ2019 በጀት ዓመት እቅድ ደግሞ በአቶ አብዲሳ ዱፌራ ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተካሂዶበታል፡፡
በእለቱ በሁለቱም ተቋማት ጥሩ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ቅንጫፍ ጽ/ቤቶች የምስጋና እና የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡
በመድረኩ ገቢዎች ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነሮች፣ እንዲሁም የሁለቱ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፈዋል።
Forwarded fromMinistry of Revenues of Ethiopia/የገቢዎች ሚኒስቴር
7
1July 29, 2026 6.5K 1 4