"ይህ ፕሮጀክት ‘ኢትዮጵያ ትበለጽጋለች’ የምንለው በተግባር እየተገነባ መሆኑን የሚያረጋግጥ ማሳያ ነው"
– የገቢዎች ሚንስትር ወ/ሮ ዓይናለም ንጉሴ
ሐምሌ 18/2018 ዓ.ም (የገቢዎች ሚኒስቴር)
የገቢዎች ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን አመራሮች በቢሾፍቱ ከተማ አቡሴራ አካባቢ በግንባታ ላይ የሚገኘውን አዲሱን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም አቀፍ ተርሚናል እና የአቪዬሽን ከተማ ፕሮጀክት ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ ወቅት የገቢዎች ሚኒስትር ወ/ሮ ዓይናለም ንጉሴ፣ "‘ኢትዮጵያ ትበለጽጋለች’ የምንለው መፈክር ብቻ ሳይሆን በተግባር እየተገነባ ያለ ሀገራዊ እውነታ መሆኑን ይህ ፕሮጀክት ያረጋግጣል" ብለዋል።
ሚኒስትሯ አክለውም ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያን የልማት አቅም፣ የህዝቦችን አንድነትና የወደፊት ተስፋ የሚያንፀባርቅ ታሪካዊ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸዋል። በልማቱ ምክንያት ከአካባቢው የተነሱ ዜጎች በተሻለ ሁኔታ ህይወታቸውን እንዲመሠርቱ መደረጉም ልማት ከማህበራዊ ፍትህ ጋር አብሮ መጓዝ እንደሚችል የሚያሳይ ተሞክሮ መሆኑን ጠቁመዋል።
እንዲህ ያሉ ለትውልድ የሚተርፉ ትልልቅ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች የኢኮኖሚ እድገትን፣ የስራ ዕድል ፈጠራን፣ የኢንቨስትመንት መስፋፋትንና የመንግስት የገቢ አቅምን በማጠናከር ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ ገልጸው፣ የገቢዎች ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽንም እነዚህን ሀገራዊ ፕሮጀክቶች በዘመናዊ የጉምሩክ አገልግሎት፣ በተቀላጠፈ የንግድ ማሳለጥ እና በውጤታማ የገቢ አስተዳደር መደገፍ ቀዳሚ ኃላፊነታቸው መሆኑን አስገንዝበዋል።
የቢሾፍቱ ከተማ ከንቲባ አቶ አለማየሁ አሰፋ በበኩላቸው፣ ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያን ራዕይ በተግባር እውን እያደረገ ያለ ታሪካዊ ስራ መሆኑን ገልጸው፣ "የዚህ ታሪካዊ ፕሮጀክት አካል መሆናችን እድለኞች ያደርገናል" ብለዋል።
በጉብኝቱ ወቅት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የፕሮጀክት ኃላፊዎች ስለፕሮጀክቱ አጠቃላይ ሁኔታ ገለጻ አቅርበዋል። በገለጻውም ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ከአህጉራዊ ተፎካካሪነት ወደ ዓለም አቀፍ መሪነት የሚያሸጋግር ስትራቴጂያዊ ፕሮጀክት መሆኑ ተገልጿል።
ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ በዓመት እስከ 110 ሚሊዮን መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም እንደሚኖረውና ከአሁኑ የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በእጅጉ የላቀ አቅም እንደሚኖረው ተጠቁሟል።
አዲሱ የአቪዬሽን ከተማ ዘመናዊ ዲጂታል አሰራሮችን፣ ግዙፍ ቀረጥ ነፃ የገበያ ማዕከላትን፣ ሰፋፊ የካርጎና የሎጂስቲክስ ማዕከላትን፣ ዘመናዊ ሆቴሎችንና ሌሎች የመሠረተ ልማት ተቋማትን ያካትታል። ይህም የንግድ ማሳለጥን፣ የውጭ ንግድ ፍሰትን፣ የጉምሩክ አገልግሎት ቅልጥፍናንና የመንግስት የገቢ አቅምን በማጠናከር ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ተገልጿል። በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ያለውን የቦታና የአቅም ማነቆ በመፍታት የኢትዮጵያን የአቪዬሽን፣ የንግድና የሎጂስቲክስ ተወዳዳሪነት በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያሳድግ ተመላክቷል።
በጉብኝቱ የገቢዎች ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዎች፣ የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር ደበሌ ቃበታ፣ ምክትል ኮሚሽነሮች፣ እንዲሁም የሁለቱ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፈዋል።
Forwarded fromMinistry of Revenues of Ethiopia/የገቢዎች ሚኒስቴር
3
1July 25, 2026 6.2K