M.O.R East Addis Ababa Branch: post #10232 — TG.ME

ብሔራዊ የታክስ ሪፎርም ታስክ ፎርስ የተቋማቱን የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸምና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድን ገመገመ

ነሐሴ 25/2018 ዓ.ም (የገቢዎች ሚኒስቴር)

በብሔራዊ የታክስ ሪፎርም ታስክ ፎርስ ሰብሳቢ ክቡር አቶ ተክለወልድ አጥናፉ ሰብሳቢነት በዛሬው እለት የገቢዎች ሚኒስቴር እና የጉምሩክ ኮሚሽን የ2018 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸምና የ2019 በጀት ዓመት የሥራ ዕቅድ ተገምግሟል።

በግምገማው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ቁጥጥርና ክትትል፣ በደረሰኝ አጠቃቀም፣ በኤክሳይዝ ታክስ አስተዳደር፣ በኢንስፔክሽን ሥራና የገቢ አሰባሰብ አፈጻጸም ዙሪያ ሰፋ ያለ ውይይት ተደርጎባቸዋል።

በኢንዱስትሪ ፓርኮች ከደረሰኝ አሰጣጥ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታት አደረጃጀት በመፍጠር የሰው ኃይል መመደቡን በመግለጽ፣ በተደረገው ክትትል የንግድ ፈቃድ ሳይኖራቸው ሲሠሩ የነበሩ ነጋዴዎች መገኘታቸው ተጠቁሟል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ቁጥጥርና ክትትል ሥራ በየሳምንቱ እየተገመገመ ሲሆን፣ የደረሰኝ አሰጣጥ ለውጥን በመለካት በገቢ ላይ ያሳየውን ተጽዕኖ በግልጽ ማሳየት እንደሚገባም ተነስቷል።

በተጨማሪም የኤክሳይዝ ታክስ የሚከፈልባቸውን ምርቶችን በቴክኖሎጂ አማካኝነት በመከታተል “Track and Trace” ለማድረግ እየተሠራ መሆኑ ተገልጿል።

የሻጮች ደረሰኝ አለመስጠትና ገዥዎች ደረሰኝ አለመቀበልን ለመቀነስ የደረሰኝ ሎተሪ ሥርዓት ለመዘርጋት የተደረገ ጥናትም ቀርቦ በአተገባበሩ ላይ ውይይት ተደርጓል።

የኢንስፔክሽን የሥራ ክፍል አስፈላጊነት ተነስቶ፣ የሥራ መመሪያዎች በአግባቡ መተግበራቸውን ለመከታተል፣ የአሠራር ቅልጥፍናን ለማሳደግ፤ ሠራተኞችንና ግብር ከፋዮችን ከስጋት የሚያወጣ አሠራር ለመፍጠር እንደሚያግዝ ተመላክቷል።

በሰሎሞን ወርቁ
ፎቶ፡- ክፍሌ አዳፍሬ
❤2
M.O.R East Addis Ababa Branch: post #10232 — TG.ME