~
በእስልምና ወንዶች በፍትህ እንዲያስተዳድሩ እንጂ፣ የልብ ፍቅርን እኩል እንዲያካፍሉ አልተገደዱም። ለምን? ምክንያቱም ፍቅር የልብ ስራ ነው፤ ሰው ደግሞ የልቡን ስሜት በፈለገው መጠን መቆጣጠር አይችልምና!
አላህ ሰውን ሲፈጥረው የልብ ዘንባሌውን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር እንደማይችል ያውቃል።
ለዚህም ነው የፍቅርና የእንክብካቤ ተምሳሌት የሆኑት ነቢዩ -ሰለሏሁ ዓለይሂ ወሰለም- ዘጠኝ ሚስቶች እያሏቸው እናታችን አዒሻን (ረ.ዐ) ከሁሉም አብልጠው ይወዷት የነበረው።
ለመሆኑ አዒሻ (ረ.ዐ) ለምን ተለየች?
ነቢዩ-ሰለሏሁ ዓለይሂ ወሰለም- ከእሷ ጋር ያሳልፉት የነበረው ጊዜ፣ እሷን የሚያንቀባርሩበትና ከሷ ጋር የሚጫወቱበት መንገድ እጅግ የተለየ ነበር። በመካከላቸው የነበረው ጥልቅ ቅርበትም አብዛኞቹ የቤት ውስጥ ሚስጥራት፣ ፍቅርንና ሮማንቲክ የሆኑ ተግባራትን የሚያመላክቱ ሀዲሶች፣ የመኝታና የገላ አስተጣጠብ ስነ-ስርዓቶች እና መሰል ግላዊ ጉዳዮች በእሷ በኩል ብቻ እንዲተላለፉ አድርጓል። ሌሎች እናቶቻችን ይህንን እድል እንደ እሷ በስፋት አላገኙም።
ታዲያ መልእክተኛው-ሰለሏሁ ዓለይሂ ወሰለም- የተራ ክፍፍላቸውን በፍትህ ካጠናቀቁ በኋላ እጃቸውን ወደ ሰማይ ዘርግተው እንዲህ ይሉ ነበር፦
«اللَّهُمَّ هَذَا قَسْمِي فِيمَا أَمْلِكُ، وَأَسْتَغْفِرُكَ لِمَا لَا أَمْلِكُ»
"ጌታዬ ሆይ! ይህ በምችለው ነገር (በጊዜና በቁሳቁስ) ያደረግኩት ፍትሃዊ ክፍፍል ነው፤ የማልችለውን (የልብ ፍቅርን) ግን ይቅር እንድትለኝ እጠይቅሃለሁ።"
ቁርአንም ይህንኑ እውነታ በግልፅ ያረጋግጥልናል፦
﴿وَلَن تَسْتَطِيعُوا أَن تَعْدِلُوا بَيْنَ النِّسَاءِ وَلَوْ حَرَصْتُمْ﴾
"በሚስቶቻችሁ መካከል (በፍቅር) እኩል ለማድረግ ምንም ያህል ብትጓጉ እንኳ አትችሉም።"
ታዲያ የባሎች ሃላፊነት ምንድን ነው?
ቁርአን ቀጥሎ ባለው አያህ የሸሪዓውን ወርቃማ ህግ ያስቀምጣል፦
﴿فَلَا تَمِيلُوا كُلَّ الْمَيْلِ فَتَذَرُوهَا كَالْمُعَلَّقَةِ﴾
"እንደ ተንጠለጠለችም አድርጋችሁ ትተዋት ዘንድ (ወደ የምትወዷት) ሙሉ በሙሉ አትዘንበሉ።" (ሱረቱን-ኒሳእ፡ 129)
አንድ ባል የፈለገውን ያህል ቢጥር ሁሉንም ሚስቶቹን እኩል መውደድ አይችልም። ይህ የአሏህ ሱና/ ህግ ነው።
ነገር ግን "ሙሉ በሙሉ መዘንበል" የተከለከለ ነው! አንዷን በፍቅር እያንበሸበሹ፣ ሌላዋን መብቷን ገፎ እንደተንጠለጠለች መተው አይፈቀድም።
ፍትህ በተግባር፣ ፍቅር ደግሞ በልብ ነው!
ስለዚህ ኡኽታህ!
ከሌሎች ሚስቶቹ ጋር በፍቅር ጦር ሜዳ ገጥመሽ፣ ጀግና ሆኖ በመገኘት የልቡን ምሽግ የመቆጣጠር ሀላፊነቱ ያንቺ ነው።
አሏህ በዚህ ጦርነት ድልን ያጎናጽፍሽ ዘንድ ምኞቴ ነው።
✍️ ወንድምሽ አህመድ ኢብኑ ዘይን
||
t.me/mirasss55
t.me/mirasss55







