የአርቲስት መኮንን ላዕከ የመኪና ውዝግብ ​ተወዳጁ አርቲስት መኮንን ላዕከ “ቃል የተገባልኝ መኪና እስካሁን… — Min Addis? — TG.ME

የአርቲስት መኮንን ላዕከ የመኪና ውዝግብ

​ተወዳጁ አርቲስት መኮንን ላዕከ “ቃል የተገባልኝ መኪና እስካሁን አልደረሰኝም” በማለት ያቀረበው ቅሬታ በዩቶፒያ ቴክኖሎጂ በኩል ምላሽ ተሰጥቶበታል። አርቲስቱ በቅርቡ በሰይፉ በኢቢኤስ ፕሮግራም ላይ የ57 ዓመት ልደቱን ካከበረበት ጊዜ አንስቶ ቃል የተገባለትን መኪና እንዳልተረከበ በይፋ መናገሩን ተከትሎ፣ ኩባንያው ስምምነቱ ለምን እንደተቋረጠ ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥቷል።

​የአሁኑ ውዝግብ መነሻ የሆነው ከአስራ አንድ ወራት በፊት በዝምታ ሬስቶራንትና ላውንጅ በተደረገው የልደት በዓል እና የዳግም ሙሽርነት ስነ-ስርዓት ላይ ነው። በወቅቱ የዩቶፒያ ቴክኖሎጂ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ አዶኒክ ወርቁ እና የድርጅቱ አምባሳደር አርቲስት እንግዳሰው ሀብቴ በቦታው ተገኝተው፣ መኪናውን ለአርቲስቱ እንደሚያመቻቹ ቃል ገብተው ነበር።

​ይሁን እንጂ የዩቶፒያ ቴክኖሎጂ ማኔጅመንት ባወጣው ይፋዊ መግለጫ፣ ጉዳዩ “ስጦታ” ሳይሆን በቅድመ-ሁኔታዎች ላይ የተመሰረተ ስምምነት እንደነበር አስታውቋል። ኩባንያው እንደገለጸው፣ ስምምነቱ የአርቲስቱን የብድር ሂደት ለመጨረስ የሚያስችል ህጋዊ ውክልና ማግኘት፣ ለመኪናው የሚያስፈልገውን ቅድመ-ክፍያ መፈጸም እና አርቲስቱ ለኩባንያው የማስተዋወቂያ ስራዎችን መስራት የሚሉ ግዴታዎችን ያካተተ ነበር።

​ኩባንያው አክሎም፣ መኪናው ለአራት ወራት ያህል በሾውሩማቸው ውስጥ ተይዞ ቢቆይም፣ አርቲስቱ እና አዘጋጅ ኮሚቴው በተባሉት ቅድመ-ሁኔታዎች መሰረት አስፈላጊውን ህጋዊ እና የገንዘብ ግዴታዎች ባለመወጣታቸው ስምምነቱን ለመሰረዝ መገደዳቸውን ገልጿል። በሌላ በኩል ዩቶፒያ ቴክኖሎጂ አሁንም ለጥበብ ማህበረሰብ ያለውን አክብሮት በመግለጽ፣ በቀጣይ ለሚገባቸው አካላት ድጋፍ የማድረጉን ስራ እንደማያቋርጥ አስታውቋል።

ፎቶ ሲሳይ ጉዛይ
@min_addis
👎14❤10🤔2😁1🤮1💔1
July 14, 2026 3.4K