ዓርብ 15/12/18
የማቴዎስ ወንጌል መልዕክት (ክፍል 50)
አርነትን ያለማጽናት አደጋው
ማቴ12:43-45
ጌታ ኢየሱስ ለፈሪሳውያንና ለሚቃወሙት ሁሉ እጅግ ትልቅ ማስጠንቀቂያ እየሰጠ ይገኛል፡፡ እርሱ ወደ ምድር የመጣው የሰውን ልጅ ነፍሰ ገዳይ ከሆነው ከሰይጣን አገዛዝ ነጻ ሊያወጣ ነው ስለዚህ ነው ዮሐንስ “የዲያብሎስን ሥራ እንዲያፈርስ የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ …” 1ዮሐ3፡9 የሚለው፡፡ ክርስቶስን የገፋና የተቃወመ ሰው ማምለጫ የለውም፡፡ በክርስቶስ ያመነ ሰው ደግሞ በህጋዊ መንገድ ከሰይጣን አገዛዝ ነጻ ወጥቶአል “እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፥ ቤዛነቱንም እርሱንም የኃጢአትን ስርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፈለሰን” ቆላ1፡13,14 ስለዚህ በክርስቶስ ያመነው ሰው ከዚህ በኋላ ሰይጣን በህይወቱ ምንም ዓይነነት ህጋዊ መብት የለውም ነገር ግን ሰይጣን ህጋዊ መብት ባይኖረውም በዚያ ሰው ህይወት ውስጥ አንዳች እድል ለማግኘት ዘወትር በዙሪያው ይዞራል “በመጠን ኑሩ ንቁም፥ ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና፤ በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት” 1ጴጥ5፡8,9 ሰው በክርስቶስ ባለው ማንነት እያደገ ካልሄደ በብዙ መንገድ እድል ስለሚያገኝ ሊያሰቃየው ይችላል ስለዚህ ራስን ከክፉ ለማዳን አማኝ በክርስቶስ ምን እንደተደረገለትና እርሱ በክርስቶስ ማን እንደሆነ እየተረዳ መሄድ ያስፈልገዋል፡፡ በዚህ ክፍል መብት ያጣው ሰይጣን ምን እንደሚያደርግ እንመለከታለን፡-
1. የመናፍስቱ ስቃይ
"ርኩስ መንፈስ ግን ከሰው በወጣ ጊዜ፥ ዕረፍት እየፈለገ ውኃ በሌለበት ቦታ ያልፋል፥ አያገኝምም" ማቴ12:43
ሰይጣንና ጭፍሮቹ በዚህ በምድር እየሰሩ ይገኛሉ፣ ይህንን የፈቀደላቸው እግዚአብሔር ሳይሆን ራሱ የሰው ልጅ ነው፡፡ ኃጢአት ምንግዜም ለሰይጣን ህጋዊ መብት ይሰጠዋል ኤፌ2፡1,2፡፡ አዳም የእግዚአብሔርን ቃል በመተላለፉ በምድር ላይ የነበረውን የመግዛት ሥልጣን ሰጥቶታል፡፡ ምንም እንኳ እግዚአብሔር የሁሉ ገዢ ቢሆንም ሰው አሳልፎ በፈቃዱ የሰጠውን ሥልጣን መንጠቅና መከልከል አይችልም ምክንያቱም ሰው ፈቃዱን በነጻነት ይጠቀም ዘንድ እንዲችል አስቀድሞ ስለሰጠው ነው፡፡ ስለዚህ ነው ክርስቶስ ራሱን በሰው ዘር ውስጥ አስገብቶ በምድር ላይ ህጋዊ መብት ያለው ሰው ሆኖ በመምጣትና ያንን ሁሉ መከራ በመቀበል የሰይጣንን ስልጣን የገፈፈው፡፡ በዚህም በመስቀሉ ስራ “አለቅነትንና ሥልጣናትን ገፎ፥ ድል በመንሣት በእርሱ እያዞራቸው በግልጥ አሳያቸው” ቆላ2፡15 ሰይጣን በምድር ላይ እንደ ሰው የሚመቸው ማደሪያ የለውም፡፡ ከሰው ከወጣ በኋላ በምድር ላይ እየተንከራተተ ይሰቃያል፡፡ ሰይጣን የግድ ማደሪያ ስለሚያስፈልገው በአንድ ወቅት ጌታ ሲያስወጣው ወደ እሪያዎች ውስጥ እንዲገቡ የለመኑት ለዚህ ነው ማር5፡12፡፡ ሰይጣን በብዙ ቁጥር ሆነውም እንኳ አብረው በአንድ ሰው ውስጥ ማደር ይፈልጋሉ፡፡ ሰይጣን ያደረበት ሰው ስቃዩ ብዙ ነው በክርስቶስ ነጻ ካልወጣ በስተቀር በሌላ በማንም ነጻ ሊወጣ አይችልም፡፡ በኃይማኖት ሰዎች የሚደረግ መናፍስትን የማስወጣት ስራ ውጤት አልባና የቀልድ ጨዋታ ብቻ ነው፡፡ ሰይጣን ድል የተነሳው በክርስቶስ ብቻ ነው፡፡
2. የመናፍስቱ ጉብኝት
"በዚያን ጊዜም፡— ‘ወደ ወጣሁበት ቤቴ እመለሳለሁ፡’ ይላል፤ ቢመጣም ባዶ ሆኖ ተጠርጎና አጊጦ ያገኘዋል" ማቴ12:44
ሰይጣን በክርስቶስ ከሰው ህይወት ከተባረረ በኋላ ስለሚሰቃይ ደጋግሞ ወደዚያ ወደ ቀድሞው ሰው እየመጣ ያየዋል ነገር ግን ያ ሰው ከዳነና ነጻ ከወጣ በኋላ ከክርስቶስ ጋር ጉዞውን ካልቀጠለ፣ በቀድሞ ድርጊቱ ከቀጠለ መንፈሱ ያንን በመጠቀም እንደገና በዚያ ሰው ህይወት ውስጥ ገብቶ የማደር መብት ያገኛል፡፡ ለአንድ ሰው ነጻ መውጣት ብቻውን ዋስትና አይደለም፡፡ አስቀድሞ የሰይጣን ተገዢ የነበረ ሰው አሁን ደግሞ የክርስቶስ ተገዢ ሆኖ ጉዞውን መቀጠል አለበት፣ የሰው ልጅ ያለ ሰይጣን ወይም ያለ እግዚአብሔር ነጻ ሆኖ መኖር አይችልም የግድ ከሁለት ለአንዱ መሆን አለበት ስለዚህ ነው ጌታ እናንተ ሸክም የከበደባችሁ ወደ እኔ ኑ አሳርፋችኋለሁ ካለ በኋላ ቀንበሬን ተሸከሙ በማለት ያዘዘው ሰው ያለ ሸክም መሆን አይችልም፡፡ የጌታን ቀሊልና ልዝብ ቀንበር እንቢ ካለ ክፉውን የሰይጣን የስቃይ ሸክም ለመሸከም ይገደዳል፡፡ አስቀድሞ ሰይጣን የገነባውን አስተሳሰብ በክርስቶስ እውቀት ካልተተካ በቀር ሰው በክርስቶስ ድኖ እንኳን ሰይጣን በነዚያ አሳቦች ይጫወትበታል ስለዚህ ነው ጌታ "... በትምህርቴ ብትጸኑ እናንተ በእውነት ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤ እውነትንም ታውቃላችሁ፤ እውነትም ነጻ ያወጣችኋል" ዮሐ8:31-32 ያለው፡፡ ስለዚህ ሰይጣን ደግሞ እድል እንዳያገኝ ሰው በክርስቶስ እውቀት መሞላት አለበት፡፤
3. የመናፍስቱ አስከፊ ድርጊት
"ከዚያ ወዲያ ይሄድና ከእርሱ የከፉትን ሰባት ሌሎችን አጋንንት ከእርሱ ጋር ይወስዳል፥ ገብተውም በዚያ ይኖራሉ፤ ለዚያም ሰው ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛው ይብስበታል። ለዚህ ክፉ ትውልድ ደግሞ እንዲሁ ይሆንበታል" ማቴ12:45
መናፍስት በግል ብቻ ሳይሆን በጋራ ተናበው ይሰራሉ፡፡ አንድ መንፈስ ከሰው ህይወት ከወጣ በኋላ ያ ሰው ዳግመኛ እድል ከሰጠው ያ መንፈስ ብቻውን አይመጣም፡፡ ሌሎች ቢያንስ በትንሹ ሰባት ከእርሱ የከፉ መናፍስትን ጋብዞ ወደዚያ ሰው ህይወት ይመጣሉ ይገቡታል የዚያም ሰው ህይወት ከቀድሞው ይልቅ የከፋ ይሆንበታል፡፡ ሰው ዳንኩ፣ አመንኩ ካለ በኋላ በጌታ ቃል መኖር ካልቀጠለ ድነቱ የጸና አይደለም፡፡ ይህንን እውነት በዮሐ8፡30-52 ባለው ክፍል ላይ አመኑ የተባሉ ሰዎች በኋላ ግን ጌታን ጋኔል አለብህ በማለት የሰደቡ እነርሱ ናቸው፡፡ አንድ ሰው ለመዳኑ ማረጋገጫ የሚሆነው ጌታን አግኝቶ ነጻ ከወጣ በኋላ ምንም ፈተናና ስደት ቢነሳበት እንኳ በክርስቶስ እውነትና ፍቅር መቀጠል ሲችል ብቻ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ካመነ ሰው ውስጥ መናፍስት እንዴት ይወጣል የሚል ጥያቄ ይነሳል፡፡ ሰው የማያውቀው ያ ሰው አመንኩ አለ እንጂ ህይወቱን ለሰይጣን አጋልጦ የሚሰጥበት የኃጢአት ወይም የሌላ አምልኮ ልምምድ ይኖረዋል እንዲሁም በጉባኤ ይታይ ይሆናል እንጂ ቃሉ በእርሱ ውስጥ የለም፡፡ ሌላው ጉዳይ ዳነ በተባለበት ወቅት ቀድሞ ከያዘው መንፈስ ነጻ አልወጣ ሊሆን ይችላል፡፡ ጌታ በነበረበት ዘመን ያለው ትውልድ ኢየሱስን በመግፋቱ የከፋ ዘመን ውስጥ ወድቋል፡፡
ጸጋ ይብዛላችሁ
Telegram:- @mentesnotkebede2020
👍 Join በማድረግ እየተቀላቀሉን ሌሎችም እንዲሳተፉ ሼር በማድረግ ይሳተፉ Email:- [email protected] ስልክ:- 0911693190
