እናንተም ተሳተፉና ተበሉ! አካውንታቸው ላይ የቀረው 59 ብር ብቻ ነው! በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ውስጥ ከ20… — 💻ᴍᴀᴍ ᴛᴇᴄʜ ᴛᴇᴄʜɴᴏʟᴏɢʏ ɪɴsᴛɪᴛᴜᴛᴇ📲 — TG.ME

እናንተም ተሳተፉና ተበሉ!


አካውንታቸው ላይ የቀረው 59 ብር ብቻ ነው!

በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ውስጥ ከ20 ዓመት በላይ ያገለገሉት ረዳት ኢንስፔክተር አንድነት ሽመልስ እና ቤተሰቦቻቸው፣ በዘመናዊ የዲጂታል ቀማኞች ወጥመድ ውስጥ ወድቀው ከ1.3 ሚሊየን ብር በላይ ተዘርፈዋል።

ጉዳዩ የተጀመረው «ቤት ቁጭ ብሎ በወር ከ70 ሺህ እስከ 100 ሺህ ብር መሥራት ይቻላል» በሚል ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በሚወጣ አታላይ ማስታወቂያ ነው። የቤት እመቤት የሆነችው ባለቤታቸው ነገሩን አምና አፕሊኬሽኑን ስትሞክረው፤ ወደ ቴሌግራም እና ዋትስአፕ ግሩፖች በመግባት «አሊባባ ኦንላይን ንግድ» በሚባል አደገኛ መዋቅር ውስጥ ትገባለች።

አጭበርባሪዎቹ ሰዎችን ለማጥመድ የተካኑ ስለሆኑ፣ እምነት ለማግኘት ሲሉ በመጀመሪያ 800 ብር ልከው 1,500 ብር ይመልሱላቸዋል። ቤተሰቡም «ነገሩ እውነት ነው» ብሎ እንዲያምን ያደርጉታል።ከዚህ በኋላ ነው እንግዲህ ትክክለኛው ሰቆቃ የሚጀምረው።

የገንዘቡ መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ሲመጣ፣ የራሳቸውን ቁጠባ ጨምሮ ከውጭ ሀገር ከምትኖር የባለቤታቸው እህት ጭምር 600,000 ብር ተበድረው ገቢ ያደርጋሉ። አጭበርባሪዎቹ ጨካኝነታቸውን አሳይተው «አንደኛ ደረጃ ነጋዴ ስለሆናችሁ ከፍተኛ ግብር መክፈል አለባችሁ» በማለት ተጨማሪ ገንዘብ እንዲያስገቡ አድርገው በድምሩ 1.3 ሚሊየን ብር እንዲዘረፉ አድርገዋቸዋል።

በሐሰተኛው መተግበሪያ ላይ 3 ሚሊየን ብር አትርፈዋል ተብሎ ይታይባቸውም ነበር፤ ነገር ግን ገንዘቡን ማውጣት ሳይችሉ ቀርተው አካውንታቸው ላይ የቀረው 59 ብር ብቻ ነው!
ይህ ሁሉ አሰቃቂ ድርጊት ሲፈጸም ረዳት ኢንስፔክተር አንድነት በሥራ ስምሪት (ፊልድ) ላይ ነበሩ። የገንዘቡን መበላት ስትሰማ የባለቤታቸው ልብ ድንጋጤን መቋቋም አቅቶት ዛሬ ላይ በጽኑ ታማ በጸበል ቦታ መንፈሳዊ ሕክምና እየተደረገላት ይገኛል። የዕድሜ ልክ ድካማቸው በአንድ ቀን ባዕድ ኃይል መናጋቱ ከፍተኛ ሐዘን ውስጥ ከቷቸዋል።

የማለዳ ቤተሰቦች ሆይ! ዛሬ ሶሻል ሚዲያ ላይ «ቀላል ገንዘብ፣ ያለ ሥራ ብዙሀብት» የሚሉ ማስታወቂያዎች በዝተዋል። ከዚህ በፊት ብዙዎችን አጥምደዋል፤ አሁንም እየጨረሱ ነው። እባካችሁ ይህንን መሬት ላይ ያለውን እውነታ ለወዳጅ ዘመድዎ በማጋራት (በማካፈል) ሕብረተሰቡ ከዚህ መሰል የዲጂታል ቀማኞች ራሱን እንዲጠብቅ ግንዛቤ እንፍጠር። የተሰበረውን ቤተሰብ ፈጣሪ ያጽናናቸው!

ማለዳ
August 9, 2026 390 2 1