‹‹ብርሃንን ፍለጋ ››
-----
መብራት ቀኑን ሙሉ ጠፍቷል።
ልጆቹ አያቶቻቸው ጋር ሄደዋል፡፡
እኩለ ቀን አካባቢ የሁለቱም ስልክ ባትሪ ሲዘጋ ምርጫ በማጣት ጥቂት ለማውራት ሞከሩ።
አልሆነላቸውም፡፡
ምሳቸውን በሚያስፈራ ጸጥታ ተከበው ከተመገቡ በኋላ ከሰል አቀጣጥላ የቀቀለችውን ስኳር ድንች እያቀረበችለት፤
"የስኳር ድንች እንጀራ እንዳለ ታውቃለህ?" አለችው፡፡
"ምን?" መለሰላት፡፡
"የስኳር ድንች እንጀራ! ሳንገባ በፊት የሼፍ ዮሃንስ ሾው ላይ ነው ያየሁት።"
"ምን ላይ?"
"ኢቢኤስ"
"እ"
"የሚገርመኝ ….እሱ ሰውዬ ግን የት ገባ?"
" እኔ ምን አውቃለሁ? ስንት የሚያስጨንቅ ነገር እያለ ደግሞ ስለ እሱ ላስብ..?"
ዝምታ።
ከአንድ ሰአት ተኩል በኋላ አየሩ መቀዝቀዝ ሲጀምር ሻይ ይፈልግ እንደሆነ ጠየቀችው።
‹‹ከሰሉ ስላልጠፋ ማፍላት እችላለሁ›› ብላ፡፡
በግዴለሽነት “እሺ” አለ።
ሻዩን ስታመጣ አብራ ኦቾሎኒ የተቀላቀለበት ቆሎ አቀረበችለትና ኦቾሎኒዎቹን ነካ ነካ እያደረገች
"ካየሁት አያስችለኝም እንጂ ኦቾሎኒ ስበላ እንደጎረምሳ ብጉር ይወረኛል…ይቅርብኝ ይሆን?›› አለችው ፡፡
አሁንም ከልቡ በማይመስል ሁኔታ፣
‹‹ይቅርብሻ ታዲያ›› አላት፡፡
ሌላ ግድንግድ ዝምታ በመሃከላቸው ወደቀ።
ከሁለት ሰአት በኋላ በበረንዳው በኩል ውጪ ውጪውን እየተመለከተች፣
"ጠቋቆረ እኮ …ዛሬ ዝናብ የሚዘንብ ይመስልሃል?" አለችው፡፡
"እንጃ። ምናልባት። ትላንት ቲክቫህ ላይ ይሄን አስር ቀን ይዘንባል የሚል ነገር አንብቤ ነበር።"
"ኦኬ…"
ከቅድሙ የገዘፈ ዝምታ።
ከደቂቃ በኋላ፣
“ይልቅ ቲክቫህ ብል…ጠዋት የሥራ ባልደረባውን በገጀራ ስለገደለ ሰውዬ ያነበብኩት ትዝ አለኝ” አላት፡፡
"ሳሊለነ ቅድስት…! ምን አድርጎት?"
"የአራስ ልጄ ጆሮ ቁርጥ የእሱን ነው ብሎ..…"
"እንዴ…?ይሄማ የለየለት እብድ ነው።"
ዝምታ።
ሰዓቱ ከምሽቱ አንድ ሰአት ሲል እና እሱ ወንበሩ ላይ ተቀምጦ ባዶ አየር ላይ ሲያፈጥ፣ እሷ ደግሞ ሶፋው ላይ ጋደም ብላ ማንጎላጀት ስትጀምር…
መብራት መጣ።
ፍሪጁ ዝዝዝዝ አለ፡፡
በርተው የተረሱ አምፖሎች ባንዴ ቤቱን ቦግ አደረጉት፡፡
ሁለቱም በእፎይታ ተንፍሰው ከመቅጽበት ብድግ አሉና ስልኮቻቸውን ከነ ቻርጀሮቻቸው ይዘው ሶኬት ወዳለበት ቦታ በተቃራኒ አቅጣጫ ተወረወሩ፡፡
13
1July 10, 2025 2.4K 4