Diinii kee Anaakara (Md Ali): post #4673 — TG.ME

የማለዳ መልእክት (45)
ለኸጢቦች እና ለዱዓቶች
~
የደዕዋ እና የኹጥባ መድረክ የነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም መድረክ ነው። የማህበረሰብን ንቃተ ህሊና ለመቀየር፣ ዲኑን ለማስተማር፣ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለማንቃት እጅግ የላቀ ቦታ ነው። ግን እንደሚገባ እየተጠቀምነው ነው ወይ? መድረኩ ነብያዊ አማና ነውና አማናውን እየተወጣን ነው ወይ? ለመድረኩ የሚመጥን አቅምና ዝግጅትስ አለን ወይ? ሐቅን ለመናገር፣ ማህበረሰብን ለመጠበቅ የሰዎችን ስሜትና ፍላጎታቸውን ተከትለን ነው የምንፈሰው ወይስ አላህን በማሰብ፣ ለሐቅ በመቆርቆር፣ ዘላቂ ጥቅምን በማስቀደም በጀግንነት እንጓዛለን? ኃላፊነትን ባለመወጣት ከመጠየቃችን በፊት ከራሳችን ጋር ሂሳብ እንስራ።

1. ወደ ህዝብ ከመቅረባችን በፊት በቂ ዝግጅት እናድርግ፣ አቅማችንን እናዳብር። ሳይዘጋጁ መቅረብ ታዳሚን መናቅ ነው። ቦታውንም ክብር ማሳጣት ነው።

2. መሰረታዊ የኢስላም ርእሶችን ቅድሚያ እንስጥ። አርካኑል ኢማን፣ አርካኑል ኢስላም፣ ተውሒድና ሺርክ፣ ሱናና ቢድዐ፣ ከባኢረ ዙኑብ፣ ስነ ምግባር፣ ኢስላማዊ ቤተሰብ፣ እንደ ኡማ ሊኖረን የሚገባ መተዛዘንና መደጋገፍ፣ ዘረኝነት፣ እንደ ጫትና ሲጋራ ያሉ ጎጂ ሱሶች፣ ወዘተ. የህዝብን ቁጣና ኩርፊያ ሳንፈራ ግን ደግሞ ባማረና በማያስበረግግ መልኩ ደጋግመን እናስተምር።

3. ርእስ መረጣ ላይ የሰዎችን ስሜትና ፍላጎት እየተከተልን አንፍሰስ። ትኩረታችን የሚጠቅማቸውን መስጠት ይሁን። ደዕዋ ሰው መለወጫ እንጂ መዝናኛ መድረክ አይደለም። የሰዎችን ስሜትና ፍላጎት እየተከተለ የሚፈስ አስተማሪ ፈሪና አስመሳይ እንጂ እውነተኛ ተቆርቋሪ አይደለም።

4. እንደ ዘመን በህዝብ ላይ የተጋረጡ አደጋዎች እና ወቅታዊ ክስተቶች ሲኖሩ አቅጣጫ መስጠት ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ በቂ ንቃትና ዝግጅት ይፈልጋል። ንቃትና ዝግጅት ማለት እንግሊዝኛ መቀላቀል አይደለም። በሚዲያ የሰማነውን ዜና ማስተጋባትም አይደለም። የዳዒ ኃላፊነት እንደ ጋዜጠኛ ክስተቶችን ማንልበልና መተንተን አይደለም። መድረኮችን የፖለቲካ መደስኮሪያ እያደረጉ ማርከስ ንቃት አይደለም። ከዳዒ የሚጠበቀው ነገሮችን በኢስላም መነፅር በመመልከት ህዝብን ማረጋጋት፣ ሰዎችን ወደ አላህ መመለስ፣ በወቅታዊ ክስተቶች ከአቅማቸው በላይ በመግባት እንዳይዋጡ ማሳሰብ ነው።

እንዳጠቃላይ ለመድረኩ የሚመጥን ትኩረት እንስጥ፤ አቅም እናዳብር፤ ዝግጅት እናድርግ፤ ጀግንነትን እንላበስ፤ ሐቀኛ ተቆርቋሪነትን ሁሌም እናስብ። ሰላም።

(ኢብኑ ሙነወር፣ ሶፈር 30/1448)
=
የቴሌግራም ቻናል፦
https://t.me/IbnuMunewor
https://t.me/IbnuMunewor
Telegram
Ibnu Munewor (ኢብኑ ሙነወር)
كناشة ابن منور
August 13, 2026 191