Diinii kee Anaakara (Md Ali): post #4667 — TG.ME

ልብህን ለማን እንደምትሰጥ እወቅ!

የዱኑያ ምሽት ላይ እንደመሆናችንና የመሲሐድ'ደጃል መምጫም እንደመቃረቡ ዲኑ ላይ የሚጫወቱና እራሳቸው ተደናብረው ኡማውን የሚያደናብሩ ሰዎች በዝተዋል።

ማህበራዊ ሚዲያውም የራሱ ጥሩ ጎን እንዳለው ሁሉ ሰዎችን ማሳሳትና ግራ ማጋባት ላይ ትልቅ አስተዋፅኦ እያደረገ ይገኛል።

መችና ከማን የሸሪዓህ እውቀት እንደተማሩ የማይታወቅ ሰዎች በካሜራ (በስልክና ኮምፒዩተር) መስኮት ብቅ እያሉ የፈለጉትን ሐላል፣ የፈለጉትን ሐራም ብለው ያለ በቂ እውቀት በስሜትና በግምት በመናገር ብዙ አላዋቂዎችን ያሳስታሉ።

ከዚህም አልፎ ገና አዲስ ወደ ኢስላም የገቡ ወንድምና እህቶች እራሳቸው እንኳ ዲኑን በትክክልና በጥልቀት ሳይረዱ መደበኛ አስተማሪ ሆነው ቀርበው ኢስላምና ሙስሊሞችን ወክለው ሲናገሩና ሲከራከሩም ይታያል !!
ይህ በጣም ይገርማል፤ ያሳዝናልም! ይበልጥ የሚገርመው ደግሞ እንደዚህ ዓይነት ሰዎችን እንደ ትልቅ አዋቂ ቆጥረው የሚከተሏቸውና ልባቸውን የሚሰጧቸው ሰዎች ሁኔታ ነው!!

ኢስላማዊ እውቀት የዲኑ/የእምነቱ አንድ አካል ነው፤ ከኔ ይሻላል ከሚሉት ሁሉ (ከየትም፣ ከማንም) እውቀትን ዝም ብሎ መቀበል እምነትን ሊያበላሽ፣ ማንነትና አስተሳሰብን ሊቀይር ይችላልና
ምላስና ድፍረት ስላለው ብቻ ራሱን በራሱ ጊዜ አስተማሪ አድርጎ የቀረበን ሁሉ ከመስማትና ከመከተል እንጠንቀቅ!!
ለአካላዊ ጤናችን ሃኪም ከምንመርጠው በላይ ለልብና ለእምነታችን መሪና መካሪ እንምረጥ።

ትልቁ መሲሐድ'ደጃል ከመምጣቱ በፊት ለሱ መንገድ የሚያመቻቹ ብዙ ትናንሽ ደጃሎች እንዳሉ ተነግሯል።

ቂያማ ሲቃረብ ሸይጣን በሰው ተመስሎ አስተማሪ ሆኖ እንደሚቀርብም ተገልጿልና ልብህን ለማን እንዳምትሰጥ/ጪ፣ የሸሪዓህ እውቀትን ከማን እንደምትቀስም/ሚ ጠንቅቀህ/ሽ እወቅ/ቂ።

የሸሪዓህ እውቀትን ከምንጩ ያልወሰደና በዑለሞች ያልተመሰከረለት የዩቱበር፣ የቲክቶከርና ፌስቡከር ... መጫወቻ እንዳትሆን/ኚ!!

ኡስታዝ አሕመድ ሸይኽ ኣደም

ዛዱል-መዓድ
©: ኡስታዝ አሕመድ ሸይኽ ኣደም
August 8, 2026 260