ክፍል 1
ፀሐፊ zoya~
..............በድቅድቅ ጨለማ ባዶ እጁን ለመግባት ሰቀቀን ይዞት ዘገም ዘገም እያለ መንገዱ እንዲረዝምለት ዱአ እያደረገ ይጓዛል። እግሮቹ ወደ ቤት ሳይሆን ወደ ተራራ የሚወጡ ይመስል ይከብዱታል። ከንፈሮቹ እህል የቀመሱም አይመስሉም፤ ደርቀውና ተሰነጣጥቀው የውስጡን ረሃብ ለከተማው አየር አጋልጠው ሰጥተዋል።
በልጅነት ህይወቱ ደስተኛ ነበር ያኔ አባቱ በህይወት እያለ የቤቱ ጣራ ሳይነቅዝ እናቱ ሳትታመም... ያኔ አለም የሱ ነበረች። አሁን ግን ይሄ ደስታ ከየት ይምጣ ደስታን ፍለጋ ሮጦ ሮጦ ዝሏል። ሥራ ፈልጎ በድካም የዛለውን ሰውነቱን ለማሳረፍ አንድ ድንጋይ ላይ ቢቀመጥ፣ መንገደኛው ሁሉ በንቀት አይን እያየ "ቦዘኔ" ብሎ ፈረጀው። በውስጡ ያለውን እሳት፣ በቤቱ ያለውን ረሃብ የሚያውቅለት አንድም ሰው አልነበረም። ሁሉም የሚፈርደው በውጪ ማንነቱ እንጂ በውስጥ ስብራቱ አልነበረም።
ሕይወት ብትመረውም፣ የጣዕሟን ፍለጋ ሲኳትን ሁለት ዓመት እንደ ቀልድ አለፈ። ሁለት ዓመት ሙሉ በቀን ስራው ተንከራተተ በየሱቁ ደጅ ቆመ፣ በየህንጻው ስር ድንጋይ ተሸከመ። ግን ድህነቱ እንደ ጥላ ተከተለው። ኪሱ ባዶ፣ ሆዱ ባዶ፣ ልቡ ደግሞ በተስፋ መቁረጥ ተሞልቷል።
ያን ቀን ምሽት መንገዱን ሆን ብሎ አቆራርጦ ሩቅ አስመስሎታል ለሱ ግን ቅርብ ነው የሰፈሩ መብራት በየተራ እየጠፋ፣ የሰው ኮቴ እየቀነሰ ነው ያለው እሱ ግን አሁንም በዝግታ ይራመዳል ወደ ቤቱ መድረሻው ጠባብ መንገድ ላይ ሲደርስ ቆመ። የቤታቸው የቆርቆሮ በር ዝገት በጨለማው ውስጥም ይታያል።
ውስጥ እናቱ እየጠበቁት እንደሆነ ያውቃል "ልጄ ምን ይዞ ይገባ ይሆን?" የሚለው የነሱ ተስፋ ለእሱ ትልቅ ጅራፍ ሆነበት። "ያ አላህ... ከዚህ በላይ ምን አይነት ፈተና አለ?" አንገቱን ወደ ሰማይ ቀና አደርጎ በጥልቀት ተመለከተ በሁለት አመት ውስጥ ጉልበቱ አልቋል፣ ክብሩ ተገፏል፣ "ቦዘኔ" የሚለው ስም ደግሞ እንደ ታፔላ ተለጥፎበታል።
በሩን ለመግፋት እጁን ሲዘረጋ፣ ከውስጥ የእህቱ የሀኪያ ደካማ ሳል ይሰማል ያ ድምፅ ልቡን ሰነጠቀው። ባዶ እጁን ገብቶ አይኖቿን ማየት ሞት ሆኖበታል እዛው ደጃፍ ላይ፣ በጨለማው ተከልሎ ለረጅም ሰአት ቁጭ ብሎ በሃሳብ ሩቅ ሄደ እንባው ከአይኑ ሳይሆን ከልቡ እየፈሰሰ...
እናቱ በሩን ከፍተው ሲወጡ በር ላይ ቁጭ ብሏል "እንዴ ልጄ መጣሃል እንዴ ምነው ብርድ ላይ?" አሉት።" አይ እማ እንዲሁ ነው"
ብሎ አልፏቸው ገባ። ሲገባ ሀኪያ አይን አይኑን እያየች
"ኦር መጣህ? ምነው ቆየህ? ማማ ተጨንቃ ነበር" አለችው ከሳሏ ጋር እየታገለች። እናቱም ቤት ገቡና ሰሃን እያወጡ
"ትንሽ የሚበላ አለ ልስጥህ?" አሉት።
"አይ እማ በልቻለሁ" አላት።
በዚህ ጊዜ ፊታቸው ተቀያየረና "አዎ ያገኘኸውን እዛው በትነህ ቆይ መች ነው የምትለወጠው? እእዕ እህትህ ታማለች እኔም ሥራ መስራት አልቻልኩም መች ነው ለቤተሰብህ የምትለፋው? ከንቱ!"ብላው ወጣች።
ከፋው... በጣም ከፋው። እንዲህ ተናግራው አታውቅም እንባውን ዋጥ አድርጎ ረሃቡን ያዝ አድርጎ አፈር በሚመስለው ፍራሽ ላይ ዘፍ አለ እንቅልፍ ወሰደው
በሩ በኃይል ይንኳኳል እናቱ ተነስታ ከፈተች። "በዚህ ሌሊት ማነው የሚያንኳኳው?" እያገረመረመች ስትከፍተው የኦርሳም ጓደኛ ኢዘዲን ነበር። አብሮ አደግ ናቸው።
"አሰላሙ አለይኩም ማዘሯ "
"ወአለይኩም ሰላም... ምነው ልጄ ሰላም አይደለም?"
"ኧረ ሁሉም አማን ነው ኦሪን ፈልጌው ነው። አዲስ ሽቀላ መጥቷል!"
ኦሪ ሽቀላ የሚለውን ቃል ሲሰማ ካለበት ፍራሽ ተስፈንጥሮ ተነሳ። እናቱ በሩ ላይ ቆመው
"ምንድነው ልጄ? በዚህ ሌሊት ምን አይነት ሽቀላ ነው?" እያሉ ቢጠይቁም ኦርሳም ግን መልስ አልሰጣቸውም።
ያቺ ከንቱ ያለችው ቃል አሁንም ልቡን እየበላችው ነው። ጫማውን ገባ አድርጎ በፍጥነት ወደ በሩ ወጣ።
"ምንድነው ኢዙ?" አለው አይኑን እያሸሸ።
ኢዘዲን
"ቶሎ በል ኦሪ! እዛ ሰፈር መጋዘን ጋ መኪና መጥታለች። ሸክም ነው ሰው እየፈለጉ ነው ቶሎ ካልደረስን ሌላ ሰው ይወስዱብናል" አለው።
ኦሪ ምንም ሳይናገር ከኢዘዲን ጋር መሮጥ ጀመረ። ሰፈሩ ጭልጭል ይላል ውሾች ይጮሃሉ። እዛው ሰፈራቸው አቅራቢያ ወዳለው ትልቅ መጋዘን ሲደርሱ አንድ ትልቅ የጭነት መኪና ቆሟል። መብራቷ ደብዘዝ ብሎ ይበራል። ወጣቶች በረድፍ ቆመው እቃ ይጫናሉ።
"አቶ በቀለ... ይሄው አንድ ሰው ይዤ መጣሁ" አለ ኢዘዲን ወደ ሹፌሩ እየተጠጋ።
ሹፌሩ አተኩሮ አየውና "ቶሎ ግባ! ይሄን ሁሉ ዱቄት ጭነን መጨረስ አለብን። ስራው ከባድ ነው መሸከም ትችላለህ?" አለው።
ኦሪ "አዎ እችላለሁ" አለ። በውስጡ ግን "ከዚህ በላይ ምን ከባድ ስራ አለ?" እያለ ነበር
ከባድ የዱቄት ኩንታሎችን በትከሻው ላይ ሲያዝል ገና መጀመሪያውኑ ሰውነቱ ተንቀጠቀጠ። ረሃቡና ድካሙ ተደራርቦበታል። ግን የሀኪያ ሳልና የእናቱ ንዴት ትዝ ሲለው ጥርሱን ነክሶ መጓዝ ጀመረ። ኩንታሉ በትከሻው ላይ ሲያርፍ አጥንቱ የሚሰበር ይመስለዋል። ላቡ በግንባሩ እየፈሰሰ ወደ መኪናው ላይ ወጥቶ ይደረድራል።
ኢዘዲንም አጠገቡ ሆኖ ያበረታታል። "አይዞህ ኦሪ... ዛሬ ይቺን ከጨረስን ጠዋት ለሀኪያ መድኃኒት ይዘህላት ትገባለህ" ይለዋል።
ሌሊቱ እየገፋ ሲሄድ የኦሪ ጉልበት እየደከመ መጣ። ሆዱ ተጣብቋል ትከሻው ቆስሏል። በአንድ በኩል ስራውን ስለሚሰራ ደስ ብሎታል በሌላ በኩል ግን "እስከ መቼ እንዲህ እሆናለሁ?" የሚለው ጥያቄ አይምሮውን ወጥሮታል።
ክፍል ሁለት.. 2 ከ 100👍 ľįķę ቡሃላ ይቀጥላል......




