በፅናት ሀገርን የሚያጸናው ሕዝባዊ ተቋም የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ጷጉሜ 03 ቀን 2018 ዓ.ም ኢትዮጵያ… — FDRE Defense Force - የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት — TG.ME

    በፅናት ሀገርን የሚያጸናው ሕዝባዊ ተቋም

የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ጷጉሜ 03 ቀን 2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ፈተናዎችን በጽናት ተሻግራ የ2018 ዓ.ም የጳጉሜን ቀናትን “የኢትዮጵያ ማንሰራራት” በሚል መሪ ቃል እያከበረች ትገኛለች።

በዚህም የጸጥታና ደህንነት ተቋማት የኢትዮጵያን የዘመናት የከፍታ ታሪክ በጽናት ለማስቀጠል ያበረከቱትን የላቀ አስተዋጽኦ ለመዘከር በማለም ዛሬ ጳጉሜን 3 “የጽናት ቀን” በሚል እየተከበረ ነው፡፡

የሀገራችን ታሪክ ከውጪ ኃይሎች ጥቃትና ከውስጣዊ ፈተናዎች ጋር ተጋፍጦ የማለፍ ውጣ ውረዶች የሞሉበት ቢሆንም፤ የኢትዮጵያ ሕዝብና መከላከያ ሠራዊት ያነገበው አይበገሬ መንፈስ ሀገሪቱን ከትውልድ ወደ ትውልድ አሻግሯታል።

በኢትዮጵያ ታሪካዊ ሂደት ውስጥ የመከላከያ ሠራዊት የሀገርና የሕዝብ ደህንነት ማረጋገጫ ግንባር ቀደም ምሰሶ ሆኖ ቆይቷል።

ዛሬም ይህንኑ አጽንቶ ለማስቀጠል የመደመር መንግሥት መከላከያ ሠራዊትን ጨምሮ የኢትዮጵያ ህልውና የሆኑ የጸጥታ ተቋማትን ትውልድ ተሻጋሪነት ለማረጋገጥ ዘመኑን በዋጀ ቴክኖሎጂ ማብቃት ትኩረት አድርጎ ቁልፍ ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል። 

ባለፉት የለውጥ ዓመታት መከላከያ ሠራዊቱ በልዩ ዘመቻዎች ኃይል፣ በአየር ኃይል፣ በሜካናይዝድ፣ በኤሌክትሮኒክስ ዋርፌርና በሳይበር ኃይሎች በምድርና በባሕር ኃይል እጅግ ሰፊና ስር ነቀል የሪፎርም ሥራዎች ተከናውነዋል።

ሠራዊቱ ራሱን በዘመናዊ የጦር መሣሪያዎች፣ በቴክኖሎጂ፣ በትምህርትና በሥልጠና በማነፅ በአሁኑ ወቅት ከኢትዮጵያ አልፎ በቀጣናው የማይናወጽ ጠንካራ ኃይል መፍጠር ችሏል።

ተቋሙ የጠላትን እንቅስቃሴ አስቀድሞ በመሰለልና መረጃ በመሰብሰብ እንዲሁም በካሚካዜ ድሮኖች የጠላትን ምሽጎች በቀላሉ የማፍረስ አቅም ፈጥሯል።

ሠራዊቱ የገነባው ይህ ኃይል በምሽግ ውጊያ ላይ ብቻ ሳይወሰን በስትራቴጂያዊ ቦታዎችና በሰላም ወረዳዎች የሚነሱ የጸጥታ ስጋቶችን በፍጥነት በመግባት ውጊያን የማጧጧፍና የጦርነትን ዕድሜ የማሳጠር ልዩ ብቃት አለው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶክተር) የጽናት ቀንን በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክት፤ ዛሬ ላይ ሀገራችን በራሷ ዕውቀትና በልጆቿ አቅም የላቀ ወታደራዊ ቴክኖሎጂዎችን መታጠቅ ችላለች ብለዋል፡፡

ብቃት ያላቸውን ሰው አልባ አውሮፕላኖችን፣ ዘመናዊ የታጠቁ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችን፣ ከባድ መሣሪያዎችንና መድፎችን እንዲሁም ተተኳሽ ጥይቶችን በራሷ ወታደራዊ ኢንዱስትሪዎች ማምረት ችላለች ነው ያሉት፡፡

ሠራዊታችን ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂን በመታጠቅ ጭምር ለሀገርና ለሕዝብ ጥቅም መረጋገጥ የማይናወጥ መሠረት መሆኑን በተግባር አስመስክሯል፤ እያስመሰከረም ይገኛል።

የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት
https://dfmc.mod.gov.et/

https://youtube.com/@fdredefenseforce-9629?si=Av-sDKCopw1FfTW2

https://t.me/+E_EOiTY9eq85ODI0

https://www.facebook.com/fdredefense.official
❤13🔥4👍2
September 8, 2026 2.2K