አልፈው ያፀኑንን ያሰብንበት ዕለት
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ጷጉሜ 03 ቀን 2018 ዓ.ም
ፅናት ለወታደር የሚታወቅበት ማንነቱ የሚለይበት መለያ ባህሪው ነው። የማይቻል የሚመስለውን ችሎ፣ የማይታለፍ የሚመስለውን ፈታኙን ቀን አልፎ ፣ ሃገርና ህዝቡን ከጥፋት ጠብቆ ከነክብሩ ከዘመን ዘመን የሚሸጋገረውና ባላንጣዎቹን በጀግንነት ተጋፍጦ ድልን የሚቀዳጀው ከአላማው ፅናት የተነሳ ነው።
መቼም ወታደርን የሚያውቅ ያውቀዋልና እንኳንስ የአመታት ትግሉ የቀን ውሎው ፅናትን ይጠይቃል ። የሃገሩን ጠላት በቁጭት ተዋግቶና እስከ እድሜው ፍፃሜ ቃሉን ጠብቆ በመኖር ትግሉ የሚጠይቀውን መስዋዕት ሁሉ እየከፈለ መፅናቱ ነው ሁሌም በተልዕኮው ድልን እንዲያስመዘግብ ያስቻለው።
በነገራችን ላይ ፅናት ማለት በራሱ የቃሉ ትርጉም ወታደር ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፤ ምክንያቱም ለአመታት ቃሉ ሳያጥፍ ፣ ካስቀመጡት ስፍራ ከቦታው የሚገኝ ፣ በእምነቱ የፀና ፣ ችግርን ተጋፍጦ ፈተናን በማለፍ ምሳሌ የሆነ ፣ ለአብነት ተጠቃሽ የፅናት ናሙና እሱ ነው።
ህዝብና ሃገሩን ከራሱ አስቀድሞ የገጠመውን ፀረ-ሰላም ሁሉ በብቃት እየተፋለመ አጥፊውን በማጥፋት ትውልድ ያስቀጠለ ባለታሪክ፤ በፅኑ ተጋድሎው በየደረሰበት ታሪክ እየሰራ የአርበኝነትን እድሜ የቀጠለ እውነተኛ የአባቶቹ ልጅ አይበገሬው የኢትዮጵያ ወታደር ነው። እናም ፅናት ሲባል ስሙ አብሮ ይጠራል።
የኢትዮጵያ ወታደር ከሃገር አልፎ የመላው አፍሪካዊ ኩራት የሆነውን ታላቁን የጥቁር ህዝቦች ድል ከነ ክብሩ ጠብቆ ያቆየውና በራሱም ዘመን ላይ ጊዜውን የሚዋጅ ገድል እየሰራ ባንዳን አስወግዶ ታሪክን ጠብቆ ያቆየ የፅናት አርማ ነው።
የኢትዮጵያ ወታደር በዘመናት ታሪኩ ውስጥ የድል አድራጊነቱ የማሸነፉና የስኬቶች ሚስጥር እድል ፣ እጣ ፈንታ ፣ አጋጣሚ ወይም ሌላ ታዕምር አይደለም በቃ ምክንያቱ አንድና አንድ ነው እሱም ፅናት ነው።
ወይም ደግሞ የፅናቱ ሚስጥር ማንነቱ ፣ ብሄር ፣ ሃይማኖቱና የዘር ሃረግ ግንዱ አይደለም፤ ፅኑ ያስባለው የጥንካሬው ምንጭ ሁሌም በድጋፍ ከጎኑ የማይለየው ሃያል ክንዱ ህዝብ ነው ።
ይሁን እንጅ ሃገርና ህዝቧን ዘመን ለማሻገር ዘመኑ ሲለወጥ ከቁጥር የጎደሉ ከገዳይ ተናንቀው በጀግንነት ወድቀው በአላማቸው ፀንተው ኢትዮጵያን ያፀኗት እልፍ ጀግኖች አሉና ይህ ቀን ሲታሰብ በዋናነት መስዋዕት የሆኑ ጓዶች ይታወሳሉ።
እነሆ ዛሬ ዕለተ ጷጉሜ የፅናት ቀን ተብላ ስለተሰየመች ጀግና እያከበረች ገድል እየዘከረች ስራ እያደነቀች በድምቀት ውላለች።
እናም በዚህ ዕለት ለዛሬ እንድንበቃ በአላማቸው ፀንተው ሽህዎች በጀግንነት መስዋዕት ስለሆኑ ዕለቱ ሲታሰብ ወድቀው ያቆሙንን አልፈው ያፀኑንን ጀግኖች አስታውሰናል።
በኤፍሬም አድማሱ
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት
https://dfmc.mod.gov.et/
https://youtube.com/@fdredefenseforce-9629?si=Av-sDKCopw1FfTW2
https://t.me/+E_EOiTY9eq85ODI0
https://www.facebook.com/fdredefense.official
20
10
10
1
1September 8, 2026 2.4K 2