ሰማይም ሀገር ነው፤ ይጠበቃል!
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ነሃሴ 29 ቀን 2018 ዓ.ም
በኢትዮጵያ አየር ኃይል ጀግኖች ዘንድ ዘወትር ሲነገር የምንሰማው አንድ ድንቅ አባባል አለ፤ “ሰማይም ሀገር ነው፤ ይጠበቃል!” ይህ አባባል ሰማይ እንደ ምድርና ባህር ሁሉ የሀገር ሉዓላዊነት አካል መሆኑን ያሳስባል። ሀገር በምድር ብቻ አትጠበቅም፤ ሰማይዋም በዘወትር ንቁ ጥበቃ ይጠበቃል።
በምድር ላይ ያለው ቴክኒሺያን በሰማይ ላይ ለሚበር ፓይለትና አውሮፕላን ደህንነት ወሳኝ መሠረት ነው። የአየር መከላከያ ሙያተኞችም “የሰከንድ መዘናጋት የዓመታት ፀፀትን ያስከትላል” በሚል እሳቤ የሰማይ ጥበቃን በከፍተኛ ንቃት ይመራሉ።
እውነትም ሰማይ የሀገር ክብር፣ የሉዓላዊነትና የደህንነት ድንበር ነው፤ እንደ ምድርና ባህር ሁሉ የራሱ ጋሻ አለዉ።
የአንበሶቹ ሰማይ
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና ተልዕኮ የሀገራችንን የአየር ክልል ከማንኛውም ጥቃት ነቅቶ መጠበቅ ነው። በበራሪዎች፣ በቴክኒሺያኖች፣ በአየር መከላከያ ሙያተኞችና በድጋፍ ሰጪ ኃይሎች የተቀናጀ ጥረት የኢትዮጵያን ሰማይ ቀንና ሌሊት በንቃት ይጠብቃል።
በምስረታ ታሪኩ ከአፍሪካ ቀዳሚ የአየር ኃይሎች አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከህዳር 20 ቀን 1928 ዓ.ም ጀምሮ በአርበኝነት፣ በጀግንነትና በመስዋዕትነት የተጻፈ አኩሪ ታሪክ ገንብቷል። የመጀመሪያዎቹ አብራሪዎች አንዱ የነበሩት ሻለቃ ሚሽካ ባብቼፍ ተቋሙን በመምራት የዚህን ታሪክ መሠረት አኑረዋል።
ከዚያ ዘመን ጀምሮ አየር ኃይሉ በሀገር ሉዓላዊነት ጥበቃ፣ በብሔራዊ ደህንነት፣ በአለም አቀፍ ሰላም ማስከበር እና በአቪዬሽን ስልጠና ዘርፍ የሚያኮራ አሻራ አሳርፏል።
የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትን በማስከበር በተለያዩ ዘመናት በተካሄዱ ጦርነቶችና የደህንነት ዘመቻዎች ወሳኝ ሚና ተጫውቷል። ከኢትዮ–ጣሊያን ጦርነት ጀምሮ እስከ ኦጋዴን ጦርነት፣ በቀይ ባህር የባህር ጥበቃ፣ በፀረ-ሽብር ዘመቻዎች፣ በባድመ ጦርነት እና በሀገር ህልውና ዘመቻዎች ድረስ የሰማይ ኃይሉ የሀገርን ክብር በተግባር አስከብሯል።
ከሀገር ውስጥ ተልዕኮው ባሻገር በዲሞክራቲክ ኮንጎ፣ በዳርፉር፣ በአብዬና በሌሎች የተባበሩት መንግስታት የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ላይ በመሳተፍ የኢትዮጵያን ሰላም ወዳድነት በአለም መድረክ አሳይቷል።
በአቪዬሽን ስልጠና ዘርፍም የራሱን የሰው ኃይል ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ለበርካታ ወዳጅ ሀገራት የአየር ኃይሎች የበረራና የአውሮፕላን ጥገና ሙያ በማስተማር የአፍሪካ የአቪዬሽን እውቀት ማዕከል ሆኗል።
በዘመናት የተፈጠሩ ችግሮች በአየር ኃይሉ የሰው ኃይል፣ የበረራ ስልጠና፣ የአውሮፕላን ጥገና፣ የትጥቅ አቅምና የአየር ትራንስፖርት ላይ ተጽዕኖ አሳድረው ነበር። ይሁን እንጂ በተደረገው ሀገራዊ ሪፎርም “ለታላቅ ሀገር ታላቅ አየር ኃይል” በሚል መሪ ቃል የአቅም ግንባታ፣ የትጥቅ ዘመናዊነት፣ የመሰረተ ልማት ማሻሻያ እና የዲጂታል ቴክኖሎጂ ሽግግር በስፋት ተከናውኗል።
ይህዛሬ አየር ኃይሉ የሰው ኃይሉን አቅም እያጎለበተ፣ የተልዕኮ ብቃቱን እያሳደገና ከአናሎግ ወደ ዲጂታል ዘመን በፍጥነት ተሻግሮ ይገኛል።
ዛሬ የኢትዮጵያ ሰማይ በንስሮች ንቃት ይጠበቃል፤ የሀገር ሉዓላዊነትም በምድር፣ በሰማይና በባህር በተቀናጀ ኃይል ይጠበቃል። ሰማይም ሀገር ነው፤ ይጠበቃል።
በፍቃዱ እሸቱ
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት
https://dfmc.mod.gov.et/
https://youtube.com/@fdredefenseforce-9629?si=Av-sDKCopw1FfTW2
https://t.me/+E_EOiTY9eq85ODI0
https://www.facebook.com/fdredefense.official
16
6
2September 4, 2026 1.7K