የመከላከያ ኮንስትራክሽንና ዲዛይን ድርጅት በመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ሙያዊ አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ነሃሴ 27 ቀን 2018 ዓ.ም
የመከላከያ ኮንስትራክሽንና ዲዛይን ድርጅት በመንገድና ሕንፃ ዲዛይን፣ በግንባታ እና በማማከር ሥራዎች በመሳተፍ ለሀገራዊ የመሠረተ ልማት አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኮሎኔል ኢንጅነር ፅጋቡ ገብረማርያም ገልጸዋል።
ኮሎኔል ፅጋቡ እንዳሉት፣ ድርጅቱ በረጅም ዓመታት ያካበተውን ሙያዊና ተቋማዊ አቅም ለመከላከያ ዘርፍና ለሀገራዊ ልማት በማዋል አቅሙን በማጠናከር ላይ ይገኛል። በዚህም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በሚከናወኑ የመሠረተ ልማት ሥራዎች ላይ በመሳተፍ ለሀገራዊ ልማት የሚጠበቅበትን ሚና እየተወጣ ነው።
ድርጅቱ እየተሳተፈባቸው ካሉት ፕሮጀክቶች መካከል የዩኒሳ–ገላን–ቢሾፍቱ–ቢዮ የመንገድ ፕሮጀክት ይገኝበታል።
በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር እየተገነባ ያለው ፕሮጀክቱ የመከላከያ ኮንስትራክሽን ዲዛይን ድርጅት በዲዛይን ማሻሻያ፣ ቁጥጥርና ማማከር ሥራዎች እየተሳተፈ ይገኛል። ለ16.5 ኪሎ ሜትር የመንገድ ግንባታው ስምንት ነጥብ አምስት ቢሊየን ብር የተመደበለትን ፕሮጀክቱ አጠቃላይ የመንገዱ ግንባታ ሰላሳ ስምንት ኪሎ ሜትር ይረዝማል።
የመንገድ ዲዛይን ቡድን መሪ ሌተናል ኮሎኔል ኢንጅነር ሙልጌታ ወርቁ እና የፕሮጀክቱ ተጠሪ መሐንዲስ ኢንጅነር ፀጋዬ ትዕዛዙ እንደገለፁት፣ ከጠቅላላው 38 ኪሎ ሜትር የፕሮጀክቱ መንገድ 8.5 ኪሎ ሜትር ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።
መንገዱ 32 ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን፣ በአንድ ጊዜ ስምንት ተሽከርካሪዎችን ለማንቀሳቀስ የሚያስችል ደረጃውን የጠበቀ መንገድ ነው። የእግረኛና የብስክሌት መንገድም በፕሮጀክቱ ዲዛይን ውስጥ ተካቷል።
ባለሙያዎቹ እንዳስረዱት፣ ፕሮጀክቱ በአንድ ዓመት ውስጥ ለማጠናቀቅ ታቅዶ የተጀመረ ሲሆን፣ በባለፉት ስድስት ወራት በዕቅዱ መሰረት እየተከናወነ ይገኛል። የአፈር ቆረጣና ሙሌት፣ የቧንቧ ዝርጋታ እና ሌሎች የመንገድ ሥራዎችም በተለያዩ የሥራ ጣቢያዎች እየተከናወኑ ነው።
የፕሮጀክቱን ግንባታ በቀጣዮቹ ስድስት ወራት ለማጠናቀቅ ቀንና ሌሊት በመሥራት ጥረት እየተደረገ ሲሆን፣ የጥራት፣ የጊዜና የበጀት መስፈርቶችን በማሟላት ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም ገልፀዋል።
ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ የትራንስፖርት ፍሰትን ከማሳለጥ ባለፈ፣ የሀገራችንን የንግድ መግቢያና መውጫ መስመሮችን በማሻሻል የንግድና የኢንዱስትሪ እንቅስቃሴን ያጎለብታል ተብሏል። በአካባቢው ያሉ ኢንዱስትሪዎችንና የኢኮኖሚ ተግባራትን በማገናኘትም ለሀገራዊ ልማት የሚኖረው አስተዋፅኦ ከፍተኛ እንደሚሆን ተገልጿል።
ዘጋቢ ብዙአየሁ ተሾመ
ፎቶግራፍ አብይ ግሩም
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት
https://dfmc.mod.gov.et/
https://youtube.com/@fdredefenseforce-9629?si=Av-sDKCopw1FfTW2
https://t.me/+E_EOiTY9eq85ODI0
https://www.facebook.com/fdredefense.official
18
16
1September 2, 2026 4K 2