ለሃገር የተሰጠ ታላቅ ክብር የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ነሃሴ 23 ቀን 2018 ዓ.ም በታሪክ አጋጣሚዎች ሁሉ… — FDRE Defense Force - የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት — TG.ME

        ለሃገር የተሰጠ ታላቅ ክብር

የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ነሃሴ 23 ቀን 2018 ዓ.ም

በታሪክ አጋጣሚዎች ሁሉ ሃገር የገጠማትን ፈተና ፊት ለፊት በመጋፈጥና በቁርጠኝነት ታግሎ በማሸነፍ የተሰጠውን ተቋማዊ  ሃላፊነት ከድሮ እስከ ዘንድሮ በፍፁም ጀግንነትና በላቀ ብቃት ተወጥቷል።

በተለይም ከውስጥና ከውጭ ሰላም ሊነሷት ታጥቀው የተነሱባትን ግጭት ናፋቂዎች በአይበገሬነት ድል ነስቶ በማንበርከክ በዘመኑ ለሃገሩ የሰራው ዘመን አይሽሬ ታሪክ በትውልድ ቅብብሎሽ ሲዘከር የሚኖር ነው። 

እድሜ ልኩን ለዓላማው ታምኖ በመቆም ፣ በግዳጅ አፈፃፀሙ ሽንፈትን ሳያስተናግድ ለዘመናት በመዝለቅ ፣ ለተልዕኮው ስኬት እስከ መስዋዕት በመፅናትና ሃገር ላይ የተፈጠረውን ምስቅልቅል ተቋቁሞ በማለፍ ቃል-አባይ በበዛበት ዘመን ውስጥ እሱ ለፈፀመው ቃል ታምኗል።

በተለይም  ኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ደራሽ በምትፈልግበት በነዚያ ፈታኝ ጊዚያቶች ፅኑ-ቃሉ ለአፍታ ሳይሻር ፣ እምነቱ ለቅፅበት ሳይጓደል ፣ ወገቡ ለደቂቃዎች ሳይላላ ፣ ትጥቁ ለሰከንድ ሳይፈታ ፣ በአቋሙ ፀንቶ በመገኘትና ከራሱ በፊት ህዝብና ሃገሩን በማስቀደም ዕሴቱን በተግባር አሳይቷል።

ዳግሞም ሃገሩ ከጥንት ጀምሮ የምትታወቅበትን የነፃነት ፣ የጀግንነትና የአርበኝነት ታሪክ ደሙን አፍስሶ ፣ ክቡር ስጋውን ቆርሶ ፣አጥንቱን ከስክሶና ውድ ህይወቱን ከፍሎ በአይበገሬነት አፅንቷል።

ስለሆነም እሱ በሃገር ግንባታ ታሪክ ውስጥ ፣ ትውልድን በማስቀጠል ሂደት ላይ አምሳያ የማይገኝለት ባለውለታ ነው። ጀግናው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት።

ሁሌም ውድ የሆነውን ለእናት ሃገሩ ለመስጠት አይሰስትም። ምክንያቱም በዘመኑ ሌላ ታሪክ የለውም። በቃ ለወታደር በነፃነት የመኖሩ ምክንያት ፣ በጀግንነት የመሰዋቱ መንስኤ ኢትዮጵያ ናት።

እርሱ ሃገር የሚታወቀው ስለ እራሱ ሲጨነቅ አይደለም። ለሰው ልጆች ሰላም መጠበቅ እድሜ ዘመኑን ሲታትር ፣ ፀረ-ሰላሞችን ለማጥፋት ሌትና ቀን ሲደክም ነው።

ድንበር ተሻግረው የሃገሩን ነፃነት ሊገዳደሩ የሚሹትን አለም አቀፍ አሸባሪዎች ሳይቀር ያሉበት ድረስ በመዝመት አይቀጡ ቅጣት ቀጥቷል።

ወረራዎችን በመቀልበስና ወራሪዎችን በማሳፈር የብረት አጥር ሆኖ ለዘመናት ዳር ድንበሩን ጠብቋል። ዛሬም ሃገራዊ ለውጡን ተከትሎ በየቦታው የተፈጠሩ የጥፋት ሃይሎችን ዕለት ቸዕለት አድኖ በመደምሰስ የውስጥ ሰላምና ደህንነትን የማረጋገጥ ተልዕኮው ላይ ትኩረት ሰጥቶ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል እየተወጣ ነው።

ወትሮም የጀግና ህይወት ለሃገር የተሰጠ በረከት ነውና የኢትዮጵያ ወታደር ከሁሉም በፊት ለሃገሩ ቅድሚያ ሰጥቶ ሰርክ ያለመታከት የሚያደርገው ያላሰለሰ ጥረት ሃገርን ከተወጠነላት የክፋት ወጥመድ እያስመለጠና ከታቀደላት የጥፋት ሴራ እየታደገ ቀጥሏል።

በኤፍሬም አድማሱ

የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት
https://dfmc.mod.gov.et/

https://youtube.com/@fdredefenseforce-9629?si=Av-sDKCopw1FfTW2

https://t.me/+E_EOiTY9eq85ODI0

https://www.facebook.com/fdredefense.official
❤26👍6👏6🔥2
August 29, 2026 4.7K 1