የቤት ኪራይ‼️
የኤሌክትሪክ ክፍያ ጨምሯል በሚል ምክንያት የቤት ኪራይ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ተከራዮች ቅሬታ አሰሙ‼️
በአዲስ አበባ ከተማ ከጊዜ ወደ ጊዜ ጭማሪ እያሳየ የመጣዉ የቤት ኪራይ ዋጋ ንረት ስጋት እንደፈጠረባቸዉ ነዋሪዎች ይናገራሉ ። በአሁኑ ወቅት የቤት ኪራይ ጭማሪ ከማሳየቱ በተጨማሪ በምንፈልገዉ ሰፈርና ለስራ ቦታችን ቅርብ በሆኑ አከባቢዎች ላይ ቤት ማግኘት ባለመቻላችን ከፍተኛ ለሆነ የትራንስፖርት ወጪ ተዳርገናል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ገልፀዋል ።
ከኢኮኖሚ አቅማችን እና ከስራ ቦታችን ጋር ቅርበት ያለዉ ቤት ለማግኘት ተቸግርናል የሚሉ ቅሬታ አቅራቢዎች እንደተናገሩት የኤሌክትሪክ ክፍያ ጨምሯል በሚል ምክንያት አከራዮች ለስቶቭና ለምጣድ የምንከፍለዉን ክፍያ ከፍ አድርገዉብናል ይላሉ ። በዚህም የተነሳ በአዲስ አበባ መሀል ከተማ በሚገኙ ሰፈሮች ቤት በጣም ዉድ በመሆኑ በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ላላቸዉ ሰዎች የማይታሰብ ነዉ ሲሉ ገልጸዋል ።
የቤት ኪራይ ዋጋ ከቦታ ቦታ ልዩነት ቢኖረውም የተሻሉ ናቸዉ ከሚባሉ አከባቢዎች አንዱ በሆነዉ በጎሮ አከባቢ ስቶቭ መጠቀም የሚቻልበት አንድ ትንሽ ክፍል ቤት እስከ 5ሺህ 500 ብር እንደሚጠየቁ የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢዎቹ እስቶቭና ምጣድ ለመጠቀም እስከ 7ሺህ ብር እንጠየቃለን ሲሉ ገልፀዋል ።
ሌላኛዉ አስተያየት ሰጪ አንደሚሉት ከሆነ የምንጠየቀዉን ክፍያ ከፍለን እንኳን በእረፍት ቀን አብዛኛዉ ሰዉ ቤት በሚቀመጥበት ቀን ከቆጣሪ መብራት የሚያጠፉ አከራዮች መኖራቸዉን ይናገራሉ ። የቤት የዋጋ ንረት እየተባባሰ መምጣት ከፍተኛ የኑሮ ጫና አሳድሮብናል የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎቸ የሚመለከተዉ አካል የዋጋ ማረጋጋት ሲራ እንዲሰራ ጠይቀዋል ።
Bisratfm








