የሕዳሴ ግድብን አንድ ሦስተኛ ኃይል የማመንጭት አቅም ያለው የኮይሻ ግድብ አፈጻጸም ከ77 በመቶ በላይ ደርሷል
+++++++++++++++++
#ጋዜጣ_ፕላስ-በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል እየተገነባ የሚገኘውና የሀገሪቱን የኤሌክትሪክ ሽፋን በከፍተኛ ደረጃ ያሳድጋል ተብሎ የሚጠበቀው የኮይሻ የውኃ ኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ አፈጻጸም ከ77 በመቶ በላይ መድረሱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሽብር ባልቻ የተቋሙን የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸምና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ለመገናኛ ብዙኃን ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት፤ ግድቡን በታቀደለት ጊዜ አጠናቆ ወደ ሥራ ለማስገባት በልዩ ትኩረት እየተሠራ ይገኛል።
በሦስት ቢሊዮን ዩሮ ወጪ ግንባታው እየተከናወነ የሚገኘው የኮይሻ የውኃ ኃይል ማመንጫ ግድብ በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ አፈጻጸሙ ከ77 በመቶ በላይ መድረሱን ተናግረዋል።
የኮይሻ ግድብን በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅና በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ደግሞ በከፊል ሥራ ለማስጀመር ግብ ተይዞ እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብን አንድ ሦስተኛ ያህል ኃይል የማመንጨት አቅም ያለው ይህ ግድብ፣ የሀገሪቱን የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነት በማሳደግ ረገድ የጎላ ሚና እንደሚኖረው ጠቁመዋል።
የኮይሻ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት በተያዘለት ጊዜ ተጠናቆ ለአገልግሎት ሲበቃ፣ የሀገሪቱን የኤሌክትሪክ ሽፋን በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግ የዜጎችን የዕለት ተዕለት ሕይወት ከመቀየር ባለፈ ለዘላቂ ልማት ትልቅ ምሰሶ እንደሚሆን ይጠበቃል።
#ጋዜጣ_ፕላስ #ኮይሻ_ግድብ #ኢትዮጵያ_ኤሌክትሪክ_ኃይል #የውኃ_ኃይል_ማመንጫ #የሕዳሴ_ግድብ #የኢትዮጵያ_ፕሬስ_ድርጅት #ኢትዮጵያ
8August 29, 2026 1.5K 1


