የጎቤ እና ሺኖዬ በዓል የአዲስ ዓመት ብስራት +++++++++++++ #ጋዜጣ_ፕላስ - የጎቤ እና የሺኖዬ በዓል… — Gazette Plus / ጋዜጣ ፕላስ/ — TG.ME

የጎቤ እና ሺኖዬ በዓል የአዲስ ዓመት ብስራት
+++++++++++++
#ጋዜጣ_ፕላስ - የጎቤ እና የሺኖዬ በዓል የአዲስ ዓመት ብስራት የሚነገርበት የወጣት ወንዶችና ልጃገረዶች ባህላዊ ጨዋታ መሆኑን የቱለማ አባ ገዳ ጌቱ ተሊላ ገለጹ።

የቱለማ አባ ገዳ ጌቱ ተሊላ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት፤ የጎቤ እና የሺኖዬ ጨዋታ በኦሮሞ ባህልና እሴት መሠረት ሊከበር የሚገባውና የዘመን መለወጫ ማብሰሪያ ባህላዊ ጨዋታ ነው።

ባህላዊ ጨዋታው ጥንታዊ የኦሮሞ ባህልና እሴቶችን የተከተለ መሆን እንዳለበት የጠቀሱት አባ ገዳ ጌቱ፤ ጎቤ እና ሺኖዬን ከባህላዊ እሴቱ ውጭ ለገቢ ማስገኛነት መጠቀም እንደማይቻል ተናግረዋል።

የጎቤ እና ሺኖዬ በዓል ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 30 ያሉ ልጃገረዶችና ወጣቶች ተሰባስበው የሚጫወቱት ባህላዊ ጨዋታ መሆኑን የገለጹት አባ ገዳው፤ በዓሉ ከጭጋጋማው የክረምት ወራት ወደ ፀደይ ብርሃን የመሸጋገሪያ ብስራት የሚበሰርበት መሆኑንም አብራርተዋል።

የዘንድሮው የጎቤ እና ሺኖዬ በዓል በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ከነሐሴ 16 ቀን ጀምሮ እየተከበረ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

ሀደ ሲንቄ ዘውዲቱ ጌታቸው በበኩላቸው፤ ጎቤ እና ሺኖዬ በመንገዶች ላይና ቤት ለቤት በመሄድ የአዲስ ዓመት ብስራት የሚነገርበት፣ እንዲሁም አንድነትና ፍቅር በአደባባይ የሚታይበት በዓል መሆኑን ገልጸዋል።

መንግሥት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት በዓሉን ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማስተላለፍ የሚረዳ መሆኑንም ሀደ ሲንቄ ዘውዲቱ አክለው ተናግረዋል።

በማርቆስ በላይ

#ጋዜጣ_ፕላስ #ጎቤና_ሺኖዬ #የኦሮሞ_ባህል #የገዳ_ሥርዓት #ኦሮሚያ #ኢፕድ #ኢትዮጵያ
❤1
August 29, 2026 1.2K 2