በድንገተኛ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ወቅት የመሠረታዊ የጤና አገልግሎቶችን ቀጣይነት ለማረጋገጥ የተዘጋጀውን መመሪያ ለማጽደቅ ወርክሾፕ ተካሄደ
በድንገተኛ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ወቅት የመሠረታዊ የጤና አገልግሎቶችን ቀጣይነት ለማረጋገጥ የተዘጋጀውን መመሪያ ለማጽደቅ እና ለማሰራጨት የሚያስችል የሦስት ቀን ወርክሾፕ ከነሐሴ 4 እስከ 6 ቀን 2018 ዓ.ም ተካሂዷል።
በወርክሾፑ የጤና ሚኒስቴር፣ የክልል ጤና ቢሮዎች፣ የክልል ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቶች፣ የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዳይሬክቶሬቶች፣ አጋር ድርጅቶች እና የዓለም ጤና ድርጅት ተወካዮች ተሳትፈዋል።
የወርክሾፑን የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ሀይሉ በድንገተኛ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ወቅት ሕብረተሰቡ መሠረታዊ የጤና አገልግሎቶችን እንዲያገኝ ማረጋገጥ የጤና ሥርዓቱ ዋነኛ ተግባር መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ በተለያዩ ወቅቶች የተለያዩ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎችን የተጋፈጠች መሆኗን ያነሱት ዶ/ር መሳይ፣ ከእነዚህም መካከል እንደ ኮቪድ-19፣ ኤምፖክስ፣ ማርበርግ፣ ወባ እና ኩፍኝ ያሉ ወረርሽኞች፣ እንዲሁም ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የተያያዙ ክስተቶችን ለአብነት አንስተዋል።
በእነዚህ የአደጋ ጊዜያት የጤና ሥርዓቱ ውጤታማ ምላሽ ለመስጠት ከፍተኛ የቅንጅት ሥራ ማከናወኑን ጠቁመው፣ ከተከናወኑት የዝግጁነትና የምላሽ ሥራዎች ጠቃሚ ልምዶችን መውሰድ መቻሉን ገልጸዋል። ከተገኙ ልምዶች በመማር የጤና ሥርዓቱን ቀጣይነትና የመቋቋም አቅም የበለጠ ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል።
እንደ ዶ/ር መሳይ ገለጻ፣ የጤና የአደጋ ሁኔታዎች ሲከስቱም በቅድመ ዝግጁነት፣ በተቀናጀ ምላሽና በጠንካራ ተቋማዊ አሠራር ወሳኝ የጤና አገልግሎቶችን ማስቀጠል ይቻላል። ይህንንም ለማረጋገጥ ኢንስቲትዩቱ ፣ የጤና ተቋማት፣ የአጋር ድርጅቶችና የሌሎች ባለድርሻዎች በትብብር መስራት ወሳኝ ነው።
በተለይም ጠንካራ የጤና ተቋማትን መገንባት፣ የጤና ባለሙያዎችን አቅምና ደህንነት ማጠናከር፣ አስፈላጊ መድኃኒቶችና የጤና ግብዓቶች በበቂ ሁኔታ መኖራቸውን ማረጋገጥ፣ የሪፈራል ሥርዓትን ማጠናከርና አማራጭ የአገልግሎት አሰጣጥ ዘዴዎችን ማቀናጀት የጤና ሥርዓቱን የመቋቋም አቅም የሚያጠናክሩ ቁልፍ ተግባራት መሆናቸውን ዶ/ር መሳይ አብራርተዋል::
የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መልካሙ አብቴ በበኩላቸው፣ በወረርሽኝ ወይም በሌላ ድንገተኛ አደጋ ወቅት ትኩረት ወደ አደጋው ምላሽ ብቻ በማድረግ መሠረታዊ የጤና አገልግሎቶች እንዳይቋረጡ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል። እንደ ዶ/ር መልካሙ ገለጻ፣ የመሠረታዊ ጤና አገልግሎቶች ሲቋረጡ ችግሩ ራሱ ወደ ሌላ የጤና አደጋ ሊቀየር ይችላል። ስለዚህ በግጭት፣ በወረርሽኝና በሌሎች የአደጋ ሁኔታዎች ወቅት መሠረታዊ የጤና አገልግሎቶች ቀጣይነት እንዲኖራቸው መመሪያው የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም የአደጋ ጊዜ የማሀበረሰብ ግንዛቤና ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው፣ ማኅበረሰቡ በአደጋ ጊዜ ምን ማድረግ እንዳለበት፣ ራሱን ከጤና አደጋዎች እንዴት መጠበቅ እንደሚችልና መቼ የጤና ተቋም መጎብኘት እንዳለበት ማስተማር እንደሚገባ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥርና የቅድመ ዝግጁነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ነኢማ ዘይኑ በበኩላቸ መመሪያው ከአደጋ መከሰት በኋላ ብቻ ሳይሆን ከወረርሽኝ ወይም ከሌላ አደጋ መጀመሪያ ጀምሮ መሠረታዊ የጤና አገልግሎቶች በምን መንገድ መቀጠል እንደሚችሉ የሚያመላክት ተግባራዊ ማዕቀፍ ለመሆን እንደተዘጋጀ ያስረዱ ሲሆን መመሪያው በተግባር ሊውል የሚችል እንዲሆን ከተሳታፊዎች የሚቀርቡ አስተያየቶችና የሥራ ልምዶች በመመሪያው የመጨረሻ ሰነድ ውስጥ እንደሚካተቱ ገልጸዋል።
አቶ እስራኤል አታሮ፣ በጤና ሚኒስቴር የማኅበረሰብ ተሳትፎና የመጀመሪያ ደረጃ ጤና እንክብካቤ መሪ ሥራ አስፈጻሚ፣ በወርክሾፑ ባስተላሊፉት መልዕክት የተሳታፊዎችን በጋራ መሥራትና የትብብር መንፈስ ላይ አጽንኦት የሰጡ ሲሆን በመተባበር አስፈላጊዎቹን የጤና አገልግሎቶች (essential services) ማስቀጠል እንደሚገባ ገልጸዋል። ይህንንም ለማረጋገጥ በጋራ መሥራትና በተቀናጀ መንገድ መንቀሳቀስ የሁሉም ኃላፊነት መሆኑን አስገንዝበዋል።
የውይይቱ ዋና ዓላማ በአደጋ ወቅት እንደ የእናቶችና ሕፃናት ጤና፣ ክትባት እና ሌሎች ወሳኝ የጤና አገልግሎቶች እንዳይቋረጡ ሊወሰዱ የሚገቡ እርምጃዎችን በግልጽ ማስቀመጥ ሲሆን ከተሳታፊዎች የሚገኙ ግብዓቶችና ምክረ ሐሳቦች ተካተው በድንገተኛ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ወቅት የመሠረታዊ የጤና አገልግሎቶችን ቀጣይነት ማረጋገጥ የሚያስችል ተግባራዊና ጠንካራ መመሪያ ለማጽደቅ ያለመ ነው።
https://ephi.gov.et/በድንገተኛ-የሕብረተሰብ-ጤና-አደጋ-ወቅት/
August 14, 2026 3.2K 4