የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የ2018 ዓ.ም. የተከናወኑ አበይት ውጤቶቹን ይፋ አደረገ
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት (EPHI) በ2018 በጀት ዓመት በሕብረተሰብ ጤና ደኅንነት፣ በበሽታ ቅኝትና ምላሽ፣ በላብራቶሪ፣ በምርምር፣ በዲጂታላይዜሽንና በጤና ስጋት ዝግጁነት ያስመዘገባቸውን ስትራቴጂያዊ ውጤቶች የሚገመግምበትንና የ2019 ዓ.ም. የተቋማዊ ግቦች ትውውቅ የሚያደርግበትን ዓመታዊ ጉባኤ የኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተሮች ፣የማኔጅመንት አባላት እና የክልል ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተሮች እና ተወካዮች በተገኙበት ማካሄድ ጀምሯል።
በጉባኤው መክፈቻ ላይ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ እንደገለጹት፤ ተቋሙ የሀገሪቱን የሕብረተሰብ ጤና እና የጤና ደኅንነት ማዕቀፍ በጥንካሬ ለማስቀጠል የተቀረጹ የፖሊሲ አቅጣጫዎችን በመከተል ተጨባጭና ውጤቶች መምጣታቸውን አረጋግጠዋል።
ኢንስቲትዩቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎችን ቀድሞ የመለየት፣ የመከላከልና ፈጣን ምላሽ የመስጠት ሀገራዊ አቅሙን በከፍተኛ ደረጃ አጠናክሯል። በዚህም በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያና በዋና ዋና የየብስ ድንበር መግቢያዎች ላይ የሚደረገውን የኢቦላ ቫይረስ በሽታ ቅኝት አጠናክሮ ማስቀጠሉን ዶ/ር መሳይ ጠቁመዋል።
አያይዘውም በኤምፖክስ (Mpox) እና በማርበርግ (Marburg) ወረርሽኞች ወቅት በተዘረጋ የተቀናጀ የምላሽ ሥርዓት በሽታዎቹ በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ መደረጉን ገልጸዋል።
የማርበርግ ወረርሽኝ ምላሽ ወቅት ከ20 ሚሊዮን በላይ የቤት ለቤት ጉብኝት፣ የበሽታ አሰሳና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች የተከናወኑ ሲሆን፣ ከ4.3 ሚሊዮን በላይ ተጓዦች በበሮች ላይ የጤና ምርመራ አግኝተዋል። የኤምፖክስና ሌሎች ወረርሽኞች ምላሽ ወቅትም ከ4.4 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የጤና ትምህርት የተሰጣቸው ሲሆን፤ በኮሌራ፣ በወባ፣ በዴንጊ፣ በማጅራት ገትርና በሌሎች ተላላፊ በሽታዎች ላይ የተቀናጀ የምላሽ ሥራ ተከናውኖ ከ3.7 ሚሊዮን በላይ ሰዎችም የኮሌራ ክትባት እንዲያገኙ ተደርጓል።
ተቋሙን የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች አስተዳደር የልቀት ማዕከል (PHEM-COE) ለማድረግ የተያዘው ዘመናዊ የዲጂታላይዜሽን ፕሮጀክት ከዝግጅት ምዕራፍ ወደ ሙሉ ትግበራ እንዳሸጋገረ የገለፁት ዳይሬክተሩ ከአጋር አካላት በተገኘ ድጋፍ 3,515 ዘመናዊ ኮምፒውተሮች ተገዝተው ለ12 ክልሎች፣ ለ2 የከተማ አስተዳደሮች፣ ለፌዴራል ፖሊስና ለመከላከያ የጤና መዋቅሮች ተሰራጭተዋል። በተጨማሪም የ830 ወረዳዎች የአደጋ ስጋት ልየታ መረጃ በSTAR ሞጁል አማካኝነት ወደ ePHEM ሥርዓት እንዲገባ ተደርጓል ብለዋል።
ዶ/ር መሳይ ኢንስቲትዩቱ በISO 15189:2022 ዓለም አቀፍ መስፈርት ላይ የተመሠረተ የጥራት አሠራርን ተግባራዊ ያደረገ ሲሆን፣ በተደረገው የቴክኒክ ድጋፍና ክትትል 10 የጤና ላብራቶሪዎች ዓለም አቀፍ የጥራት እውቅና (Accreditation) ማግኘታቸውን ገልፀዋል። 125 ላብራቶሪዎች በSLIPTA ፕሮግራም ሥር ድጋፍና ክትትል ያገኙ እንደሆነ እና፣ የBLQMS ትግበራም በሀገር ደረጃ 86 በመቶ መድረሱን ጠቁመው በዓመቱ 683,320 የሪፈራል ናሙናዎች በመደበኛና በአማራጭ የትራንስፖርት መንገዶች በተገቢው ጥንቃቄ መጓጓዛቸውን ገልፀዋል።
በሳይንሳዊ ምርምር ዘርፍ አመርቂ ውጤት እየመጣ እንደሆነ እና ኢንስቲትዩቱ 127 የምርምር ውጤቶችን በታዋቂ ዓለም አቀፍ ሳይንሳዊ ጆርናሎች ላይ ማሳተሙን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ለ49 የምርምር ጥናቶች ደግሞ ቴክኒካል ሪፖርት መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ ጥናቶቹ በሥርዓተ ምግብ፣ በጤና ሥርዓት፣ በተላላፊና ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ላይ ያተኮሩ ሲሆን፣ የምርምር ጥራታቸውና ተአማኒነታቸው በገለልተኛ አካላት በኩል ዓለም አቀፍ መስፈርቱን ማሟላታቸው ተረጋግጧል።
በተጨማሪም የEMIS 2025 ሰርቬይ በይፋ ተጀምሮ የመረጃ ሰብሳቢዎች ሥልጠና ተጠናቆ ወደ መስክ የተሰማሩ ሲሆን፣ የምርምር ሥነ-ምግባር ቦርድ (IRB) ፕሮፖዛሎችን በዲጂታል ሥርዓት መገምገም መጀመሩ የምርምር ሥነ-ምግባር ክትትል ሂደቱን አዝምኖታል።
ኢንስቲትዩቱ በብሔራዊ የጤና ደኅንነት የድርጊት መርሃ ግብር (NAPHS) እና በ«አንድ ጤና» (One Health) ማዕቀፍ አማካኝነት የብዝሃ-ዘርፍ ትብብርን ያጠናከረ ሲሆን፣ በበርካታ ዓለም አቀፍ የሕብረተሰብ ጤና መድረኮችና ከፍተኛ ደረጃ ጉብኝቶች በመሳተፍ የሁለትዮሽና የብዙ ወገን ስትራቴጂያዊ አጋርነቱን አጠናከረ ዶ/ር መሳይ በንግግራቸው አውስተዋል።
ዶ/ር መሳይ በመጨረሻም የ2018 ዓ.ም. ስኬቶች ኢንስቲትዩቱ ከምርምርና መረጃ ማመንጨት ጀምሮ እስከ ላብራቶሪ አቅም ማጠናከር፣ ወረርሽኝ መቆጣጠርና ፈጣን ምላሽ መስጠት ድረስ ያለውን ብሔራዊ መሪነት የሚያረጋግጡ ሲሆን በዚህ ጉባኤው በ2018 ዓ.ም. የተመዘገቡ አፈጻጸሞችንና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በዝርዝር በመገምገም፣ በ2019 ዓ.ም. የተቋሙን ተልዕኮ በበለጠ ውጤታማነት ለማሳካት የሚያስችሉ ሀገራዊ ዕቅዶችን በመወያየትና በማጽደቅ ይጠናቀቃል ብለዋል።
www.ephi.gov.et/ኢንስቲትዩቱ-የ2018-ዓ-ም-የተከናወኑ-አበይት/
www.facebook.com/share/p/1DFeBaJSjQ/
https://x.com/i/status/2094388577954078834
August 31, 2026 754