ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለተውጣጡ የጤና ባለሙያዎች በመሰረታዊ የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ስልጠና እውቅና… — Ethiopian Public Health Institute | የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት — TG.ME

ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለተውጣጡ የጤና ባለሙያዎች በመሰረታዊ የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ስልጠና እውቅና ተሰጣቸው
------------------------
ከአዲስ አበባ የተለያዩ ወረዳዎች የተውጣጡ 37 የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ባለሙያዎች የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ዝግጁነት ዳይሬክቶሬት ከኢንስቲትዩቱ የስልጠና ማዕከል ጋር በመሆን የሰጠውን የመሰረታዊ የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ስልጠና (Frontline Field Epidemiology Training Program) አጠናቀው ተመርቀዋል።

አቶ ዳንኤል ዳምጠው የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር እንዲሁም የምርምር ዳይሬክተር አሁን ስልጠናቸውን ያጠናቀቁ ባለሙያዎች የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ላይ ያላቸውን አቅም ይበልጥ የገነቡ ሲሆን ይህንንም አቅም በስራቸው በመተግበር ለሕብረተሰቡ የሚሰጡትን አገልግሎት ጥራት እንደሚያጎለብተው ገልጸው በቀጣይም እውቅና ካገኙት ባለሙያዎች መካከል አብላጫ ውጤት ያመጡት ቀጣዩን የመካከለኛ (Intermediate) ከዛም በተመሳሳይ ሁኔታ ከፍተኛ (Advanced) FETP ስልጠናዎችን የመሰልጠን እድል እንደሚመቻችላቸው ገልጸዋል።

በኢንስቲትዩቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር በዝግጁነት ዳይሬክቶሬት የፈጣን ምላሽ ቡድን አስተዳድር ዲቪዥን ሃላፊ ዶ/ር መልካሙ አስራት ስልጠናው የተሰጠው በጽንሰ ሀሳብ ብቻ ሳይሆን ተግባርንም ያካተተ በመሆኑ ባለሙያዎቹ በስራቸው ላይ ያላቸውን የጤና አደጋዎችን የመለየት፣ የመከላከል እና የመቆጣጠር አቅማቸውን የሚያዳብር መሆኑን የገለጹ ሲሆን ወ/ሮ እናኑ ሁነኛው የኢንስቲትዩቱ የስልጠና ማዕከል ተጠባባቂ ዳይሬክተር በበኩላቸው የስልጠናው የስልጠና መመሪያዎች (training manuals) ከወቅቱ ጋር እንዲስተጋበሩ በቅርቡም ተሻሽለው እንደሚቀርቡ ተናግረዋል።

የኢንስቲትዩቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ዝግጁነት ዳይሬክቶሬት ባለሙያና የስልጠናው አስተባባሪ አቶ አወል ዳውድ እንዳስረዱት ኢንስቲትዩቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር አቅምን ለማሳደግ ስልጠናውን ተደራሽ በማድረግ ላይ ሲሆን የአሁኖቹን ተመራቂዎች ጨምሮ ከ235 በላይ ከአዲስ አባባ የመጡ ባለሙያዎች ስልጠናውን ወስደዋል። ስልጠናው የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቀድሞ የመለየት የመከላከልና ምላሽ የመስጠት ግንዛቤ እንዲሁም መሰረታዊ የኮምፒውተር ሞያዎች ጨምሮ ለባለሙያዎች በስፋት መሰጠቱን ተናግረዋል።
https://ephi.gov.et/ከአዲስ-አበባ-ከተማ-አስተዳደር-ለተውጣጡ/
https://x.com/i/status/2094421949090836661
https://www.facebook.com/share/p/19Ny2EwX2X/
August 31, 2026 533 2