አልማዝ ባለጭራ Herpes zoster ━━✦━━ አልማዝ ባለጭራ (Herpes zoster) ህመም በቆዳ ላይ… — ከስነ-ፅሁፍ ዓለም — TG.ME

አልማዝ ባለጭራ
Herpes zoster
━━✦━━

አልማዝ ባለጭራ (Herpes zoster) ህመም በቆዳ ላይ የሚወጣ ሽፍታ ያለው ሕመም ሲሆን ቫሪሴላ - ዞስተር (Varicella zoster) በሚባል ቫይረስ አማካኝነት ይከሠሰታል። ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ 20 በመቶ የሚሆነው የዓለማችን ህዝብ በዚህ በሽታ ይጠቃል። ይህ ሕመም የሚከሠሰተው አስቀድሞ ጉድፍ (Chickenpox) በተያዙ ሰዎች ላይ ነው።

አልማዝ ባለጭራ እንዴት ይከሠሰታል?

ቫሪሴላ - ዞስተር ሰዎች በጉድፍ እንዲታመሙ የሚያደርግ ቫይረስ ሲሆን፤ ሕመሙ ካለፈ በኋላ ይህ ቫይረስ በአከርካሪ እና በአንጎል አቅራቢያ በሚገኙ ነርቮች ውስጥ ይቀመጣል። አመቺ ሁኔታን ሲያገኝ ይህ ቫይረስ በነርቮች ውስጥ በመጓዝ በቆዳ ላይ አልማዝ ባለጭራ በሽታ እንዲከሠሰት ያደርጋል።

ለአልማዝ ባለጭራ (Herpes zoster) አጋላጭ ምክንያቶች

➢ ኤች. አይ. ቪ. ኤድስ ህመም
➢ የካንሰር በሽታ ወይም የኬሞቴራፒ ሕክምና
➢ አንዳንድ መድኃኒቶች (Steroids)
➢ ከፍተኛ ውጥረት ወይም ጭንቀት

የአልማዝ ባለጭራ ምልክቶች

➢ አልማዝ ባለጭራ ማንኛውንም የሰውነት ክፍል ሊያጠቃ ይችላል። አብዛኛውን ጊዜ ግን በአንድ ጎን በኩል በደረት፣ በሆድ ወይም በጀርባ ላይ ሲወጣ ይስተዋላል።

➢ ይህ ህመም ቆዳ ላይ ሽፍታ ከማሳየቱ ጥቂት ቀናት አስቀድሞ የመደንዘዝ፣ የማቃጠል እና የማሳከክ ስሜት ይኖረዋል። ይህ ስሜት ከታየ 1 ወይም 2 ቀናት በኋላ በአንድ የሰውነት ጎን ብቻ የቆዳ መቆጣት እና የቀበቶ ቅርፅ የመሰለ ውሃ የቋጠረ፣ ሕመም ያለው ሽፍታ መታየት ይጀምራል። ብዙ ጊዜ ሽፍታው ከጥቂት ቀናት በኋላ መድረቅ እና መክሰም ይጀምራል። ከዚያም በአንድ ወይም ሁለት ሳምንት ውስጥ ይጠፋል።

➢ በተጨማሪ ትኩሳት ፣ ድካም፣ ራስ ምታት እና ሕመሙ በተከሰተበት አካባቢ ንፍፊት (Lymphadenopathy) መውጣት ሊኖር ይችላል።

አልማዝ ባለጭራ ተላላፊ ነውን?

ታማሚዎች በቀጥታ አልማዝ ባለጭራን ማስተላለፍ አይችሉም። ነገር ግን የጉድፍ ክትባት ያልወሰደ ወይም ጉድፍ ታምሞ የማያውቅ ሰው በታማሚው አካባቢ በሚሆንበት ጊዜ በጉድፍ በሽታ ሊጠቃ ይችላል። ቫይረሱ ከታማሚው ሰው ጋር በሚደረግ ቀጥታ የቆዳ ንክኪ ወይም በትንፋሽ አማካኝነት ይተላለፋል።

ስለዚህ የጉድፍ ክትባት ያልወሰደ ወይም ጭራሽ ታምሞ የማያውቅ ሰው ከታማሚው ጋር የቅርብ ንክኪ ባያደርግ ይመረጣል።

የአልማዝ ባለጭራ (Herpes zoster)
ምርመራዎች ምንድን ናቸው?


የጤና ባለሙያዎች ሽፍታውን በማየት እና ስለምልክቶቹ በመጠየቅ ስለበሽታው መረዳት ይችላሉ። እንዲሁም ከሽፍታው ላይ ናሙና በመውሰድ ምርመራ ሊደረግ ይችላል።

የአልማዝ ባለጭራ (Herpes zoster) ሕክምና

➢ በቤት ውስጥ የሚደረግ ሕክምና
➢ ሽፍታው የአለበትን አካባቢ ንጽሕፅህና መጠበቅ
➢ በተጨማሪም እርጥበት እንዳይኖር በጥንቃቄ ማድረግ
➢ ቆዳን የበለጠ ሊጎዱት ስለሚችሉ እርጥበት ያላቸውን ቅባቶች እና ክሬሞችን ማስወገድ
➢ የተመጣጠነ ምግብ መመገብ፣ በቂ ዕረፍት ማድረግ
➢ ሰፋ ያሉ እና ምቾትን የሚሰጡ ልብሶችን መልበስ
➢ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ማድረግ፣ ውጥረትን መቀነስ

በሕክምና ተቋማት ውስጥ የሚደረጉ ሕክምናዎች

➢ የፀረ -ቫይረስ መድኃኒቶች፤ ፣ እነዚህ መድኃኒቶች የቫይረሱን መራባት ለማገድ፣ የሕመሙን ክብደት እና ቆይታ ለመቀነስ እና ሽፍታው በፍጥነት እንዲድን ለማድረግ ያግዛሉ። በተለይም ሽፍታው በተከሠሰተ በ72 ሰዓታት ውስጥ መወሰድ ከተጀመሩ ውጤታቸው ጥሩ ይሆናል።

አልማዝ ባለጭራ (Herpes zoster) መከላከያ መንገዶች

➢ ሕፃናት የጉድፍ መከላከያ ክትባትን እንዲወስዱ ማድረግ
➢ በአደጉት አገራት ዕድሜያቸው ከ50 ዓመት በላይ ለሆኑ ሰዎች የአልማዝ ባለጭራ መከላከያ ክትባትን እንዲወስዱ ይደረጋል።
➢ የአልማዝ ባለጭራ ታማሚዎች እስኪያገግሙ ድረስ ርቀትን መጠበቅ ያስፈልጋል። በተለይም የጉድፍ ክትባትን ካልወሰዱ ወይም በጉድፍ ተይዘው የማያውቁ ከሆነ ይህን ማድረግ ጠቃሚ ይሆናል።
━━━━━━━━━━━
ምንጭ ➢ NBC ETHIOPIA
📖 📖 📖 📖 📖
https://t.me/Ethiobooks
Telegram
ከስነ-ፅሁፍ ዓለም
✍ አዝናኝ፣ አስተማሪና ቁም ነገር የሚያስጨብጡ የብዕር ውጤቶች የሚቀርቡበት የናንተው ቻናል! የቻናላችን https://t.me/Ethiobooks ቤተሰብ ሁኑ፣ ለወዳጅ ጓደኞቻችሁም 'share' አድርጉ። ለአስተያየት፣ ስነ-ፅሁፋዊ ጥቆማና ማስታወቂያ @firaolbm እና @tekletsadikK ተጠቀሙ።
👍4
September 2, 2026 562