አልበርት ቺኑዋ አልሞጉ አቼቤ እ.ኤ.አ. ኖቬምበር 16 ቀን 1930 ዓ.ም. በምሥራቃዊቷ የናይጄሪያ ግዛት… — ከስነ-ፅሁፍ ዓለም — TG.ME

አልበርት ቺኑዋ አልሞጉ አቼቤ እ.ኤ.አ. ኖቬምበር 16 ቀን 1930 ዓ.ም. በምሥራቃዊቷ የናይጄሪያ ግዛት ኢግቦላንድ፣ አውጊዲ ከተማ ውስጥ ከስድስት ልጆች መካከል አምስተኛ ሆኖ ነው የተወለደው።

በወቅቱ አካባቢውን ያስተዳድሩ የነበሩ የብሪታኒያ መንግሥት ወኪሎች ወላጆቹ ትውፊታዊውን የኢግቦ እምነት ትተው ክርስትናን እንዲከተሉ አሳምነዋቸዋል። በመሆኑም አቼቤ በክርስትና ልማድ ነው ያደገው። ሆኖም ስለ ናይጄሪያ ነባር እምነቶች ጉጉት መቋጠሩ አልቀረም።

በመንግሥታዊው የኡሞሃያ ኮሌጅ ከመማሩም ባለፈ ከኢባዳን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በ1954 ዓ.ም. ተመርቋል። ጆሴፍ ኮንራድን የመሳሰሉ ስመጥር ብሪታንያዊ ደራሲያን ስለ አፍሪካ የከተቧቸውን ሥነ-ጽሑፋዊ ድርሳናት ባነበበ ቁጥር እጅግ ይከፋው ነበር።

አውሮፓውያኑ ስለ አፍሪካውያኑ የሚያቀርቡት ገለጻ ተደጋግሞ ልክነት ከማጣቱም በላይ ገፀ-ባህርይ አቀራረጻቸውም ቅያሜን የሚፈጥር ዓይነት ይሆኑበታል።

ስለዚህም በ1959 ዓ.ም. በናይጄሪያ የዜና ማሰራጫ ተቋም በሚሠራበት ወቅት የመጀመሪያ ልቦለዱን "Things Fall Apart"ን ጽፎ አሳተመ። መጽሐፉ ወዲያውኑ ዓለም አቀፋዊ ዝናን አስገኘለት።

በተከታታይም በ1960 "No Longer at Ease" ፣ በ1964 ደግሞ "Arrow of God" የተባሉ ሥራዎቹን እንካችሁ አለ። በነዚህ ድርሰቶቹም ነባሩ የአፍሪካ ባህል ከምዕራብ ቀመሱ ዘመናዊነት ጋር የተጋባውን ግጭት ያሳያል።

በ1960ዎቹ አጋማሽ ናይጄሪያ የነፃነት ወረቷ ተንጠፍጥፎ አልቆ መራር እውነቷ እየገጠጠ፣ እርስ በርስ መናናቁና መጨቋቆኑም እየበረታ በመጣበት በዚህ ወቅት፣ ማለትም በ1966 የአንድ አጭበርባሪ የአገሪቱ ፖለቲከኛን ውጣ ውረዶች የሚያትተውን "A Man of the People" ን ጻፈ።

አቼቤ ፖለቲካዊ ጽሑፎችን ከማሳተም በዘለለ በፖለቲካው መልክእ ምድር ውስጥ ቀጥተኛ ተሳትፎም ነበረው። በድርሰቶቹም የሕዝቡን ተግዳሮቶችና ተስፋዎች ማንፀባረቅን ግብ አድርጓል። የቢያፍራ ግዛት ራሷን ከቀረው ናይጄሪያ ለመገንጠል ሙከራ ባደረገችባቸው ከ1967 - 1970 ባሉት ዓመታት የቢያፍራ ወኪል በመሆን በተለያዩ የዓለም ሀገራት ተዘዋውሮ ጉዳዩን ለማስረዳትና ድጋፍ ለማሰባሰብ ጥሯል።

የየጋዜጣውንና የየመጽሔቱን ገፆች የቢያፍራን ትግል በሚያስረዱ መጣጥፎች ከማጨናነቁም በላይ ሙሉ ትኩረቱን ለዚሁ ዓላማ ሰጥቶ ረዘም ካለ ፈጠራዊ ሥነ-ጽሑፍ ርቋል። በ1969 ዓ.ም. በሰጠው ቃለ መጠይቅም ያለበት ሁናቴ ረዥም ልቦለድ ለመጻፍ እንደሚያስቸግረውና ግፋ ቢል ሥነ-ግጥም ብቻ ሊጽፍ እንደሚችል ተናግሮ ነበር።

በዚያን ወቅት በእርግጥም ሦስት የሥነ-ግጥም ቅፆችን አሳትሟል። የአጫጭር ልቦለዶች ስብስብና የሕፃናት ታሪኮችንም ወደ አንባቢው አድርሷል። የቢያፍራ ራስን የመቻል ትግል በክሽፈት ከተደመደመ በኋላ አቼቤ በ"ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ናይጄሪያ" በማስተማር ቆይቷል።

ከ1992 ዓ.ም. አንስቶ ለጥቂት ዓመታት ወደ ዩ. ኤስ. አሜሪካ አቅንቶ በተለያዩ ዩኒቨርሰቲዎች ሲያስየምር ከቆየ በኋላ በ1976 ዓ.ም. ወደ ናይጄሪያ ዩኒቨርሲቲ ተመልሷል።

በ1987 ዓ.ም. ለሕትመት የበቃው "Anthills of the Savannah" የተሰኘው ድርሰቱ የስልጣን ጥማትን ጭብጥ አድርጎ የተዋቀረ ነው። እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ ፕሬዝዳንት ለመሆን የሻተ ፖለቲከኛን መዘዞች ይተርካል። የመጽሐፉን ሕትመት ተከትሎም ዳግም ወደ አሜሪካ ተጉዟል። በአጠቃላይ አቼቤ በሕይወት ዘመኑ 162 መጻሕፍትን ለአባቢያን አበርክቷል።

በ1990 ዓ.ም. ወደ አገሩ ተመልሶ ሳለ ያጋጠመው የመኪና አደጋ ከወገቡ በታች መንቀሳቀስ እንዲሳነው አድርጎታል። ቺኑዋ አቼቤ ማርች 21 ቀን በ2013 ዓ.ም. በ82 ዓመቱ በአሜሪካ - ቦስተን ከተማ ሕይወቱ አልፏል።
━━━━━━━━
ምንጭ ➢ ድረ-ገጽ
📖 📖 📖 📖 📖
https://t.me/Ethiobooks
Telegram
ከስነ-ፅሁፍ ዓለም
✍ አዝናኝ፣ አስተማሪና ቁም ነገር የሚያስጨብጡ የብዕር ውጤቶች የሚቀርቡበት የናንተው ቻናል! የቻናላችን https://t.me/Ethiobooks ቤተሰብ ሁኑ፣ ለወዳጅ ጓደኞቻችሁም 'share' አድርጉ። ለአስተያየት፣ ስነ-ፅሁፋዊ ጥቆማና ማስታወቂያ @firaolbm እና @tekletsadikK ተጠቀሙ።
👍4🤔3
August 31, 2026 539 3