የድምጻዊ ማሕሙድ አሕመድ አዲስ አልበም
የአንጋፋው ድምጻዊ ማሕሙድ አሕመድ «ለታሪክ» የተሰኘውንና የኪነ-ጥበብ ሕይወቱ ማጠቃለያ የሆነውን 26ኛ አዲስ የሙዚቃ አልበሙን ሊለቀቅ እንደሆነ ተሰምቷል።
ላለፉት ስድስት አሰርት ዓመታት በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ ደማቅ አሻራ ያኖረው አርቲስቱ፤ ይህንን አልበም ያዘጋጀው የቀደሙትን የሀገር ውስጥ የሙዚቃ ቅርሶች ሳይበረዙና ሳይለወጡ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ በማሰብ እንደሆነ ገልጿል።
አልበሙ 13 ትራኮችን የያዘ ሲሆን ዘመናዊ የሙዚቃ መሣሪያዎችን ከባህላዊ የቅኝት ድምፆች ጋር ያዋሐደ ፤ ይዘቱም ትውልድን፣ ፍቅርን፣ ሀገርን፣ የሕይወት ፍልስፍናን እና ማኅበራዊ እሴቶችን የሚያንጸባርቁ ግጥሞችን አካቷል።
በርካታ ወጣትና አንጋፋ የሙዚቃ አቀናባሪዎች የተሳተፉበት የጋሽ መሐሙድ የመጨረሻ አልበም ሲሆን፤ አዲሱ ትውልድ የሀገሩን ባህልና ማንነት ሳይለቅ በዘመናዊነቱ እንዲቀጥልበት ጥሪ አቅርቧል።
ይሳቃል ኢንተርቴይመንት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅና ለማሰራጨት ኃላፊነቱን የወሰደው ይህ አልበም፤ በቅርቡ በSpotify፣ Apple Music፣ YouTube እና በሌሎችም ዲጂታል መድረኮች ላይ ለሕዝብ ክፍት የሚሆን ሲሆን፣ ከአልበሙ የተመረጠ አንድ ነጠላ ዜማ ለአዲስ ዓመት ዋዜማ ለአድማጮች እንደሚለቀቅ ታውቋል።


















