አትፍሩ ፡፡ከብዙ ድንቢጦች እናንተ ትበልጣላችሁ።
ሁለት ድንቢጦች በአምስት ሳንቲም ይሸጡ የለምን? ከእነርሱም አንዲቱ ያለ አባታችሁ ፈቃድ በምድር ላይ አትወድቅም።
የእናንተስ የራሳችሁ ጠጕር ሁሉ እንኳ ተቈጥሮአል።
እንግዲህ አትፍሩ ከብዙ ድንቢጦች እናንተ ትበልጣላችሁ ( ማቴ 10 ÷ 29 - 31 ) ።
ማብራሪያ
ድንቢጥ ልዩ ልዩ መልክ ያለው አነስተኛ ወፍ ነው፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲያስተምር የሁለት ድንቢጦች ( ወፎች ) ዋጋ ስንት እንደሆነ ነገራቸው፡፡
ከእነዚህ ድንቢጦች ያለ እርሱ ፈቃድ አንዲቱም ብትሆን አትጠፋም፡፡ አምላካችን ለእነዚህ ድንቢጦች እንኳ የሚጠነቀቅ ነው፡፡ ሁለት ድንቢጦች በአምስት ሳንቲም መሸጣቸውን ያወሳ አምላክ የኛንም ጓዳ ጎድጓዳ ምን ያህል እንደሚያውቅ ያሳየናል፡፡
ጠጕራችን መቆጠሩን ስናነብ ምን ተሰማን? እግዚአብሔር የማያውቀው ነገር የለም፡፡ ሁሉ ነገራችንን ያውቃል፡፡ የራስ ጠጕራችንን ቁጥር ሳይቀር ያውቃል፡፡
አንድ ሰው በድርጅቱ ውስጥ ያሉትን ንብረቶቹን ያውቃቸዋል፡፡ ቆጥሮም ያስቀምጣል፡፡ ዋና ዋና ስለምንለው ነገራችን ይቅርና የራስ ጠጉራችንን ቁጥር ሳይቀር እግዚአብሔር የሚያውቅ አምላክ ነው፡፡
አትፍሩም ተብለናል፡፡
አትፍሩ ማለቱ አትጨነቁ ለማለት ነው፡፡ መጨነቅ ደግሞ የሌለብን እንዴት እንደሆነ ልንገራችሁ፡፡ የጠጕራችንን ቁጥር ለማወቅ አስጨንቆን ያውቃል? አስጨንቆን አያውቅም፡፡ የጠጕራችንን ቁጥር ማወቅ ለምን አላስጨነቀንም? በርግጥ የጠጕራችንን ቁጥር ማወቅ አያስጨንቅም፡፡ ስለ ጠጕራችን ቍጥር መጨነቅ የሚያስፈልግ ነገር አይደለም፡፡ የሚገርመው ግን ስለ ምንም ነገር እንዳንጨነቅ ተነግሮናል፡፡ ስለ ጠጕራችን ቁጥር መጨነቅ የሚያስፈልግ ነገር እንዳልሆነ ሁሉ ስለ ሌላውም ( ስለምንጨነቅለት ነገር ) መጨነቅ እንደማያስፈልግ ተነግሮናል ( ማቴ 6÷ 25 - 32 ) ፡፡
በእግዚአብሔር ዘንድ የራሳችን ጠጕር ሁሉ እንኳ መቆጠሩ የኛ ማንኛውም ጉዳይ በእርሱ ዘንድ እንዴት ትኵረት እንደሚሰጠው ያሳያል፡፡
አንዲቱም ድንቢጥ ያለ አባታችን ፈቃድ አትወድቅም፡፡ የኛም ማንኛውም ነገር እግዚአብሔር ሳያውቀው የሚሆን ነገር የለም፡፡
ራሱም እንዳለው ከብዙ ድንቢጦች እናንተ ትበልጣላችሁ። ይህ ማለት ለድንቢጦቹ ከተጠነቀቀ ከድንቢጦች ለምንበልጠው ለኛ አብዝቶ ይጠነቀቅልናል ማለት ነው፡፡ አትፍሩ የተባልነውንም መርሳት የለብንም፡፡
ከእግዚአብሔር ጋር መኖር ማለት ያለ ጭንቀት መኖር ማለት ነው፡፡ ቢያስጨንቀን እንኳ ጉዳዩን ለእግዚእብሔር በመስጠት ከጭንቀት ነጻ ሆነን የምንኖርበት ኑሮ ነው፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡ አሜን!
✍ ዘማሪ ዲያቆን ንጉሤ ጥላሁን ( ወንጌል ሰባኪ ) በተጨማሪም የንድፍና የኮምፒዩተር ባለሙያ
▶️ ስብከቶቼንና መዝሙሮቼን በዩቱቤ ቻናል ማግኘት ትችላላችሁ
https://youtube.com/channel/UC5CXetEDzzsnMHbPAT-b_0w
▶️ ቴሌግራም ቻናል
https://t.me/EMaweq
▶️ ፌስቡክ
fb.me/yeglie









