የወልዲያ ማከፋፈያ ጣቢያ በዛሬው ዕለት በስኬት ኢነርጃይዝ ተደረገ …….///……. የባህር ዳር - ወልዲያ… — EEP Communication — TG.ME

የወልዲያ ማከፋፈያ ጣቢያ በዛሬው ዕለት በስኬት ኢነርጃይዝ ተደረገ
…….///…….
የባህር ዳር - ወልዲያ - ኮምቦልቻ ባለ 400 ኪሎ ቮልት የማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክት አካል የሆነው የወልዲያ ባለ 230 ኪሎ ቮልት ማከፋፈያ ጣቢያ በዛሬው ዕለት ኢነርጃይዝ ተደርጓል።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የትራንስሚሽን ቢዝነስ የፕሮግራም 1 ፕሪጀክት አስተዳደር 1 ቢሮ ሥራ አስኪያጅ አቶ አሸናፊ ሙሉብርሃን እንደገለፁት ማከፋፈያ ጣቢያው የፕሮጀክቱ አካል ከሆነው የ 7 ነጥብ 5 ኪ.ሜ  ባለ 230 ኪሎ ቮልት መስመር ላይ ኃይል እንዲያገኝ ተደርጓል፡፡

የወልዲያ ማከፋፈያ ጣቢያ መስከረም 2018 ዓ.ም ላይ የፍተሻ ስራ በአብዛኛው ተጠናቆ የነበረ ቢሆንም በወሩ መጨረሻ ላይ በአካባቢው በተቀሰቀሰ ግጭት የተነሳ በጣቢያው የተተከሉ ዕቃዎች ጉዳት ደርሶባቸው ሥራውን የሚያከናውነው ተቋራጭ ፕሮጀክቱን አልቀጥልም እስከማለት ደርሶ እንደነበር አቶ አሸናፊ ተናግረዋል፡፡

ይሁንና በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የትራንስሚሽን ቢዝነስ ዘርፍ እና የፕሮጀክት ቢሮው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ቀሪውን ሥራ የተቋሙ ባለሙያዎች ሥራውን ከተቋራጩ በመረከብ ኢነርጃይዝ ማድረግ ትልቅ ስኬት ማስመዝገብ ተችሏል ብለዋል።

እንደ አቶ አሸናፊ ገለፃ የባህር ዳር - ወልዲያ - ኮምቦልቻ ባለ 400 ኪሎ ቮልት የማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክት አካል የሆነው 300 ኪ.ሜ የሚረዝመው ከባህር ዳር - ወልዲያ የተዘረጋው ባለ 400 ኪ.ቮ የማስተላለፊያ መስመርም የፍተሻ ሥራ በመካሄድ ላይ ነው፡፡

በቅርቡ ፍተሻው ሲጠናቀቅ ዝግጁ ከተደረገው የወልዲያ ባለ 400 ኪሎ ቮልት ስዊትችጊር ጋር እንደሚገናኝ ጠቁመዋል።

የባህር ዳር - ወልዲያ - ኮምቦልቻ የማስተላለፊያ መስመርና የማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክት ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ ኮምቦልቻ ላይ ያለውን ኢንዱስትሪ ፓርክ እንዲሁም በወልዲያ እና ኮምቦልቻ ከተሞች እና አካባቢያቸው አስተማማኝ ኃይል እንዲያገኙ ያደርጋል።

በማይመች ሁኔታ ላይ ሥራቸውን ከፍተኛ መስዋዕትነት ላከናወኑ ለተቋሙ ሠራተኞች እና አመራሮች ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ፕሮጀክቱ በተደጋጋሚ ከጸጥታ እና ስርቆት እንዲሁም በሰሜን ኢትዮጵያ ተካሂዶ ከነበረው ጦርነት ጋር በተያያዘ የፕሮጀክት ዕቃዎች መጥፋት እና መጎዳት አጋጥሞት እንደነበር መግለፃችን ይታወሳል፡፡

💡 "ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

📌ፌስቡክ↠https://www.facebook.com/Ethioelectric
📌ቴሌግራም↠https://t.me/EEPCommuication
📌ሊንክዲን↠ https://www.linkedin.com/company/ethiopian-electric-power
📌ዩትዩብ↠https://www.youtube.com/@ethiopowermedia
📌ድረ- ገጽ ይጎብኙ https://www.eep.com.et
ነሐሴ 23 ቀን 2018 ዓ.ም
❤21👏9⚡1
August 29, 2026 4.1K 5