ወይ ስምህን ወይም ደግሞ አመልህን ቀይር!
ታዋቂው ታላቁ አሌክሳንደር (Alexander The Great) በዘመኑ በውን የሚታወቀውን አብዛኛውን የአለም አካባቢ በታላቅ ሰራዊቱ በቁጥጥር ስር እንዳዋለ የሚነገርለት ዝነኛ ሰው ነበር፡፡ አንድ ጊዜ ለጦር ዝግጅት በማድረግ ላይ እንዳሉ በሌሊት በሰራዊቱ መካከል ለመዘዋወር ሲወጣ ተረኛ የነበረ አንድ ጠባቂ አንቀላፍቶ አገኘው፡፡ በወቅቱ ተረኛ ሆኖ ያንቀላፋ ጠባቂ የሞት ፍርድ ይጠብቀዋል፡፡ ታላቁ አሌክሳንደር ወደወታደሩ ሲጠጋ ወታደሩ በመንቃት ላይ ነበረና የሆነውን ነገር ሲያውቅ ሕይወቱን እንደሚያስከፍለው ስላሰበ በጣም ፈራ፡፡
ታላቁ አሌክሳንደር ለወታደሩ፡- “የጥበቃ ተረኛ ሆኖ ማንቀላፋት በምን እንደሚያስቀጣ ታውቃለህ?” አለው፡፡ ወታደሩ ድምጹና ሰውነቱ በፍርሃት እየተንቀጠቀጡ፣ “አዎን አውቃለሁ” አለው፡፡
ታላቁ አሌክሳንደርም ለወታደሩ፡- “ስምህ ማን ነው?” አለው፡፡ ወታደሩ፡- “ስሜ አሌክሳንደር” ይባላል” አለው፡፡
ታላቁ አሌክሳንደር እንደገና ለወታደሩ:- “ስምህ ማን ነው?” አለው፡፡ ወታደሩ አሁንም “ስሜ አሌክሳንደር ይባላል” ብሎ ደግሞ መለሰ፡፡
ታላቁ አሌክሳንደር ለሶስተኛ ጊዜ ጮክ ብሎ ወታደሩን፣ “ስምህ ማን ነው?” ብሎ ጠየቀው፡፡ ወታደሩም ለሶስተኛ ጊዜ፣ “ስሜ አሌክሳንደር ይባላል” ብሎ መለሰ፡፡
ታላቁ አሌክሳንደር ወታደሩን ትኩር ብሎና አፍጥጦ እየተመለከተው፣ “ወይ ስምህን ቀይር ወይም ደግሞ አመልህን ቀይር” አለው ይባላል (ምንጭ፡- Snopes.com)፡፡
ራሱ በትጋቱና በዲሲፕሊኑ የሚታወቀው ታላቁ አሌክሳንደር በስም ሞክሼው የሆነው ወታደር የሱን ስም ይዞ በአመሉ ግን ቸልተኛና እንቅልፋም መሆኑ ስላበሳጨው ነው “ስምህና አመልህ ስለማይመሳሰል አንዱን ቀይር” የሚልን መልእክት ያስተላለፈለት፡፡
በዘመናችን ሁላችንንም የሚያታግለን ችግር በላያችን ላይ የለጠፍነው ስም ከአመላችንና ከተግባራችን ጋር አብሮ ያለመሄድ ችግር ነው፡፡ ወንድም፣ ፍቅረኛ፣ የሃገር ዜጋ፣ የሕዝብ አገልጋይ፣ ሕዝብ ጠባቂ፣ መሪ . . . የሚሰጡንና የምንሸከማቸው ስሞች አስገራሚ ናቸው፡፡ ሆኖም፣ ስማችንና አመላችን (ተግባራችን) አብሮ ካልሄደ አንዱን መቀየር የግድ ነው፡፡
ስምህ “ወንድም” ከሆነ ወይ የወንድም አመል ይኑርህ አለዚያ አንደኛህን ስምህን ቀይር!
ስምህ “ፍቅረኛ” ከሆነ ወይ የፍቅረኛ አመልና ባህሪይ ይኑርህ አለዚያ አንደኛህን ስምህን ቀይር!
ስምህ “የሐገር ዜጋ” ከሆነ ወይ እንደ ጨዋ የሐገር ዜጋ መልካም አመል ይኑርህ አለዚያ አንደኛህን ስምህን (ዜግነትህን) ቀይር!
ስምህ “የሕዝብ አገልጋይ” ከሆነ ወይ ትሁት፣ ሕዝብ አክባሪና ጨዋ አመል ይኑርህ አለዚያ ስምህንና የስራ ዘርፍህን ቀይር!
ስምህ “የሕዝብ ጠባቂ” ከሆነ ንቁ፣ በጥቅም የማይደለልና ለሕዝቡ ሲል ራሱን የሚሰዋ ጠባቂ ሁን አለዚያ ስምህንና የስራ ዘርፍህን ቀይር!
ስምህ “መሪ” ከሆነ ወይ ራስን መርቶ ሌላውን በምሳሌ የሚመራ አመልና ዲሲፕሊን ይኑርህ አለዚያ አንደኛህን ስምህን ቀይር!
ስምህ ማን ነው? ሹመትህ ምንድን ነው? ስልጣንህ ምንድን ነው? ስራህ ምንድን ነው? ከሰዎች ጋር ያለህ ግንኙነት ምንድን ነው? ወይ ያንን ኑር አለዚያ አንደኛህን ስምህን፣ ስራህን፣ ዘርፍህንና የግንኙነትህን መልክ ቀይር!
ወይ ስምህን ወደ አመልህና ወደተግባርህ አምጣው፣ ወይም አመልህንና ተግባርህን ወደስምህ ውሰደውና አንድ አይነት ሁን! በአጭሩ፣ ሰው ሁን!!!
https://t.me/Dreyob
https://m.youtube.com/user/naeleyob623
https://www.facebook.com/Dr-Eyob-Mamo-1050816404958639/
Telegram
Dr. Eyob Mamo
Life skill development!
You can contact me
@DrEyobmamo

53
11
11August 27, 2026 6.3K 7 22