ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የከተማ አስተዳደሩን ምክር ቤት ስትራቴጂካዊ ፕላን ለማዘጋጀት የሚያስችል የምክክር መድረክ አካሄደ
የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት ቀጣይ የስራ አቅጣጫውን የሚያመላክት ስትራቴጂካዊ ፕላን (strategic plan) ለማዘጋጀት የሚያስችለውን የመነሻ ሰነድ ይፋ አድርጓል። የሚዘጋጀውን ሰነድ አስመልክቶም ከድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር መስራት የሚያስችለውን ምክክር ከዩኒቨርሲቲው ተወካዮች ጋር አካሂዷል፡፡
በዚሁ የምክክር መድረክ ላይ የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ የተከበሩ አቶ አብዲ ሙክታር፣ ምክትል አፈ ጉባኤ የተከበሩ ወ/ሮ ከሪማ አሊ፣ የምክር ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ አመራሮች፣ የዘርፉ ባለሙያዎችና መምህራን ተሳትፈዋል።
ይህ በእውቀትና በምርምር ላይ የተመሠረተ የስትራቴጂክ ፕላን ዝግጅት የምክር ቤቱን የአሰራር ዘይቤ በዘመናዊ መንገድ ለማዋቀር፣ አገልግሎት አሰጣጥን ለማቀላጠፍና ተቋማዊ አቅምን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ተመልክቷል።
የሰነድ ዝግጅቱን በስኬትና በታቀደለት የጥራት ደረጃ ለማጠናቀቅ ይቻል ዘንድ ከድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ እና ከምክር ቤቱ የተውጣጡ ባለሙያዎችና አመራሮች የተካተቱበት አብይ ኮሚቴ እና ንኡስ ኮሚቴ ተቋቁመው ቀጥታ ወደ ተግባራዊ የስራ እንቅስቃሴ መግባታቸውም ተገልጿል።
በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ የተከበሩ አቶ አብዲ ሙክታር ባስተላለፉት መልዕክት፣ የስትራቴጂክ ፕላን ዝግጅት ስራው በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ እና የጥራት መስፈርቶች መሰረት ተሰርቶ እንዲጠናቀቅ አሳስበዋል፡፡
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በአስተዳደሩ ስር ለሚገኙ ተቋማት ዘርፈ ብዙ ድጋፎችን እያደረገ ሲሆን ተቋማት በሚያቀርቡት ጥያቄ እና የትብብር ስራዎች ማዕቀፍ መሰረት መሰል ደጋፎችን መድረጉን እንደሚቀጥል ተመላክቷል፡፡
6September 4, 2026 2.5K 1





