የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ለ200 ወጣቶች የሥራ ፈጠራና የአስተሳሰብ ለውጥ ላይ ትኩረቱን ያደረገ ሥልጠና መስጠት ጀመረ
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በማኅበረሰብ ተሳትፎ ዳይሬክቶሬት አማካኝነት የሚያካሂደው የ2018 ዓ.ም. የክረምት በጎ ፈቃደኝነት መርሃ ግብር አካል የሆነውን የወጣቶች አቅም ግንባታ ሥልጠና ዛሬ ማስጀመሩን አስታወቀ።
ከተለያዩ ወረዳዎች የተውጣጡ 200 ወጣቶች የሚሳተፉበት ይህ ሥልጠና፤ በሥራ ፈጠራ (Entrepreneurship) እና በአስተሳሰብ ለውጥ (Mindset Change) ላይ ያተኮረ ነው። ሥልጠናው ወጣቶች የራሳቸውን እምቅ አቅም እንዲረዱ፣ የሥራ ፈጠራ ክህሎታቸውን እንዲያሳድጉ፣ ግልጽ ግብ በማስቀመጥ በተግዳሮቶች ውስጥ አዳዲስ ዕድሎችን የመመልከት አዎንታዊ አስተሳሰብ እንዲገነቡ ለማስቻል ታስቦ እንደተዘጋጀ ተጠቁሟል፡፡
በሥልጠናው ወቅት ተሳታፊዎች በሥራ ፈጠራ መሠረታዊ እውቀቶች ላይ ከሚኖራቸው ግንዛቤ በተጨማሪ በራስ መተማመን፣ ተጠያቂነት፣ ችግር ፈቺነት፣ ጽናት እና የወደፊት ዕቅድ ዝግጅት ላይ ተግባራዊ ልምዶችን የሚያስጨብጡ ትምህርቶች ይሰጣቸዋል።
ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በዚህ አቅም የመገንባት ተነሳሽነቱ፤ ወጣቶች በሥራ ፈጠራ እንዲሰማሩና በአካባቢያቸው ሁለንተናዊ ልማት ላይ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ለራሳቸው እንዲሁም ለመጡበት ማኅበረሰብ ተጨማሪ እሴት እንዲፈጥሩ ለማስቻል በማሰብ ስልጠናውን እንዳዘጋጀ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ስልጠናው ለሁለት ተከታታይ ቀናት ከፍተኛ ልምድ ባላቸው የዩኒቨርሲቲው ምሁራን አማካኝነት እነደሚሰጥ ተጠቁሟል፡፡
21
3September 3, 2026 3K 6







