በአርቲስት ኡስማዮ ሙሳ ህይወት ታሪክ ዙሪያ የተፃፈ መፅሐፍ ዛሬ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ተመረቀ
የታዋቂውን አርቲስት ኡስማዮ ሙሳ የህይወት ታሪክ የሚያስቃኝ እና በአርቲስቱ የመጀመሪያ ልጅ አርቲስት ሳርቱ ኡስማዮ የተፃፈ መጽሐፍ የድሬዳዋ አስተዳደር ከፍተኛ የመንግስት ሀላፊዎች፣ የዩኒቨርሲቲው አመራር እና ጥሪ የተደረገላቸው ታዋቂ አርቲስቶች በተገኙበት ተመርቋል፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ክቡር አቶ አብዲ ሙክታር በመርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት፣ አርቲስት ኡስማዮ ለኦሮሞ የሙዚቃ እና ስነ ጥበብ እድገት ካበረከተው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ባልተናነሰ መልኩ ለህዝቦች እኩልነት፣ ነፃነት እና አንድነት ታሪክ የሚዘክረው አሻራ ያኖረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ለህዝብ እኩለነት ዋጋ የከፈሉ ጀግኖች እንዲታወሱ የሚያደርገውን ጥረት ያደነቁት ክቡር አቶ አብዲ፣ ታላላቅ የማህበረሰቡ መሪዎች እና ፋና ወጊ የነፃነት ታጋዮች እንዲታወሱ ፣ አበርክቷቸው ለትውልድ አንዲተላለፍ ታሪካቸው በመፅሐፍ መልክ ተሰንዶ ለአንባቢወ መድረስ አለበት ብለዋል፡፡
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም በበኩላቸው፣ በምስራቁ የሀገራችን ክፍል ለትውልድ የሚተላለፉ ታሪኮችን በመፅሐፍ መልክ አዘጋጅቶ የማቅረብ ልምድ ያልዳበረ መሆኑን ገልፀው በአርቲስት ኡስማዮ ታሪክ ዙሪያ የተዘጋጀው መፅሐፍ በብዙ መልኩ አስተማሪ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልፀዋል፡፡ መፅሐፉ በአርቲስቱ ሴት ልጅ መዘጋጀቱ ሴት ፀሐፊያንን ከማበረታታት ባሻገር የህዝብ ታሪክ፣ ባህል እና ቋንቋ እድገት ጉልህ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል፡፡
የአርቲስት ኡስማዮ ሙሳ ልጅ እና የመፅሐፉ ፀሐፊ አርቲስት ሳርቱ ኡስማዮ በመፅሐፉ መመረቅ የተሰማትን ደስታ ገልጻለች



















