የውሃ ስርጭት እና ተደራሽነትን ማሻሻል የሚያስችል የስራ ውል ከአስተዳደሩ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ጋር ተደረገ… — Dire-Dawa University — TG.ME

የውሃ ስርጭት እና ተደራሽነትን ማሻሻል የሚያስችል የስራ ውል ከአስተዳደሩ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ጋር ተደረገ

በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ ያለውን የውሃ ስርጭት ችግር በቋሚነት መፍታት የሚያስችል የስራ ስምምነት ከድሬዳዋ አስተዳደር ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ጋር ተፈርሟል።

ዩኒቨርሲቲው የውሃ እጥረት ችግርን መቅረፍ የሚያስችሉ የከርሰ ምድር ውሃ ቢያስቆፍርም የስርጭት ክፍተት በመኖሩ ምክንያት በተማሪዎች መኖሪያ፣ በቢሮዎች እና የመምህራን መኖሪያ ቤቶች አካባቢ የውሃ ስርጭት እጥረት ተከስቷል። ከአስተዳደሩ ውሃ እና ፍሳሽ ባለስልጥን ጋር የተደረገው ስምምነት ይህንኑ የውሃ ስርጭት ችግር በዘላቂነት የሚቀርፍ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡

በሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቀው ይህ ፕሮጀክት፣ በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ እና በመምህራን መኖሪያ አካባቢዎች የሚስተዋለውን የአቅርቦት ችግር እንደሚያቃልል ተገልጿል።

በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ላይ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም እንደገለጹት ‘’የድሬዳዋ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ፕሮጀክቱን በወቅቱ በማጠናቀቅ በተቋም ደረጃ የሚስተዋለውን የውሃ ስርጭት ተግዳሮት ለማቃለል የተለመደ ድጋፉን እንዲያደርግ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት አክለውም ባለስልጣኑ በቀጣይም ግቢውን የማስዋብ እና የባለሙያዎችን አቅም በማሳደግ ረገድ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በትብብር እንዲሰራ ጠይቀዋል፡፡።

የድሬዳዋ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር መሀመድ ሙሴ በበኩላቸው ‘’ዩኒቨርሲቲው በራሱ ጥረት እያከናወናቸው ያሉትን የልማት ስራዎችን አድንቀዋል። አቶ መሀመድ አክለውም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የተጀመረውን የውሃ ስርጭት ፕሮጀክት ከተያዘለት ጊዜ ቀድሞ ለማጠናቀቅ ተገቢውን አመራር እንደሚሰጡ ገልጸዋል።
❤32👏8😴3
August 15, 2026 8.7K 10