Defence Construction Enterprise: post #2171 — TG.ME

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የአዋሽ ሰባት መሠረታዊ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ማዕከል ግንባታ ፕሮጀክት የመስክ ምልከታ ተካሄደ

ሐምሌ 27 ቀን 2018 ዓ.ም.

በመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ ግንባታው እየተከናወነ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የአዋሽ ሰባት መሠረታዊ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ማዕከል ግንባታ ፕሮጀክት ላይ የመስክ ምልከታ ተካሄደ።

በምልከታው ላይ የመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ብርጋዴር ጄኔራል ኢንጂነር ሰጠኝ ሊኪሳ እና የኢንተርፕራይዙ የሕንጻ ግንባታ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸናፊ ሐሰን ተገኝተው የፕሮጀክቱ ሥራ አፈጻጸም በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳና በጥራት እየቀጠለ መሆኑን ተመልክተዋል።

የኢንተርፕራይዙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ቀሪዎቹን ሥራዎች በተያዘለት ጊዜ አጠናቀን ለባለቤቱ ለኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ በፍጥነት ጨርሶ ለማስረከብ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የአዋሽ ሰባት ማሰልጠኛ ማዕከል ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ኮሎኔል ኢንጂነር እሸቱ ታደሰ በግንባታው ሂደት ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ሥራ አስኪያጁ እንዳሉት፤ በአሁኑ ወቅት የጣሪያ፣ የበርና መስኮት ገጠማ፣ የኤሌክትሪክ፣ የሳኒተሪ እና የመንገድ ሥራዎችን ጨምሮ ቀሪ ሥራዎች በፍጥነት እየተከናወኑ ይገኛሉ። የግንባታ ፕሮጀክቱ የሚገኝበት አካባቢ ከፍተኛ ሙቀትና የዲዛይን ማስተካከያዎች ቢኖሩበትም፤ የሥራ ሰዓትን እንደየአየር ሁኔታው በማስተካከል፣ እንዲሁም የሰው ኃይልና ቁሳቁሶችን በማሟላት ሥራው ያለምንም ማቋረጥ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

የማሰልጠኛ ማዕከሉ ግንባታ ሲጠናቀቅ፤ ለ4,200 ሰልጣኞች የሚሆን መኖሪያ፣ ለ900 ሰልጣኞች የሚሆን መመገቢያና ዘመናዊ የምግብ ማዘጋጃ፣ 100 የአሰልጣኞች እና 10 የመኮንኖች መኖሪያዎች፣ 8 የቢሮ ሕንጻዎች፣ ሁለገብ መጋዘን፣ መጸዳጃ ቤቶች፣ የጥበቃ ቢሮ፣ የግቢ አጥርና በር፣ ለሰልጣኞች የምረቃ አገልግሎት የሚሰጥ መድረክ እንዲሁም ከመሠረተ ልማት ጋር የተያያዙ መንገዶችን ያካትታል።
❤11
August 3, 2026 1.9K 1