ዝክረ_ቅዱሳን_ነሃሴ_፲፫/13 እንኳን ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ደብረ ታቦር በሰላም አደረሳችሁ… — "፩ እምነት" ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ Channel — TG.ME

#ዝክረ_ቅዱሳን_ነሃሴ_፲፫/13

እንኳን ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ደብረ ታቦር በሰላም አደረሳችሁ አደረሰን

ደብረ ታቦር

➱ደብረ ታቦር በቁሙ እሥራኤል ውስጥ ከሚገኙ ተራሮች አንዱ ነው:: ተራራው ብዙ ታሪካዊ ዳራዎች ቢኖሩትም ክብሩ ከፍ ከፍ ያለው ግን ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን ስለ ገለጸበት ነው:: ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-

➱አካላዊ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋችንን በተዋሐደባት በዚያች በተወደደች ጊዜ: ደቀ መዛሙርቱ ስለ እግዚአብሔር መንግስት ምሥጢርን ይማሩ ነበር በጊዜው ግን አበው ሐዋርያት ምሥጢር ባይገባቸው: አንድም ገና መንፈስ ቅዱስ በእነርሱ ላይ አልወረደም ነበርና እምነታቸው ሙሉ አልነበረም::

➱ጌታም አምላክነቱን በየጊዜው በቃልም: በተግባርም ይገልጥላቸው ነበር በርግጥ ያንን ነደ እሳት: ሰማያት የማይቸሉትን ግሩማዊ አምላክ በትሑት ሰብዕና መመልከቱ ሊከብድ እንደሚችል መገመት አያዳግትም::

➱ጌታችን ብዙ ተአምራትን በአምላካዊ ጥበቡ ሠርቷል እጅግ ድንቅ ከሆኑት መካከል ደግሞ ቅድሚያውን ደብረ ታቦር ይይዛል ጌታ ስለ ምን መለኮታዊ ክብሩን በደብረ ታቦር ገለጸ ቢሉ:-
፩.ትንቢቱ ሊፈጸም (መዝ. 88:12)
፪.ምሳሌው ሊፈጸም (ባርቅና ዲቦራ በሢሣራ ላይ ድልን ተቀዳጅተዋልና)

፫.ሊቀ ነቢያት ሙሴ "ልይህ" ብሎ ከ1,500 ዓመታት በፊት ጠይቆ ነበርና እርሱን ለመፈጸም
፬.አንድነቱን: ሦስትነቱን ለመግለጽ
፭.ቤተ ክርስቲያንን በምሳሌ ለማሳየት
፮.ተራራውን ለመቀደስ
፯.የሐዋርያቱን ልብ ለማጽናት . . . ወዘተ ነው::

➯ነሐሴ 7 ቀን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ወደ ቂሣርያ ፊልዾስ ወስዶ "የሰውን ልጅ ማን ይሉታል?" ብሎ ጠይቁዋቸው ነበር እነርሱም የራሳቸውን ሐሳብ የሌላ እያስመሰሉ "አንዳንዶቹ ኤልያስ: አንዳንዶቹም ሙሴ: ሌሎቹም ከነቢያት አንዱ ነው ይሉሃል" አሉት::

➯ኩላሊትን የሚመረምር ፈጣሪ ነውና "እናንተስ ማን ትሉኛላችሁ?" ቢላቸው ደንግጠው ዝም አሉ የሃይማኖት አባት: ባለ በጐ ሽምግልና ቅዱስ ዼጥሮስ ግን በመካከላቸው ቆሞ "አንተ ውዕቱ ክርስቶስ ወልደ እግዚአብሔር ሕያው - የሕያው እግዚአብሔር አንድያ የባሕርይ ልጁ ክርስቶስ አንተ ነህ" አለው:: በዚያን ጊዜ ቃለ-ብጽዓን እና የመንግስተ ሰማያት መክፈቻ ተሰጠው:: (ማቴ. 16:13)

➯መጽሐፍ እንደሚል ደግሞ እንዲህ ከሆነ ከ6ኛው ቀን በሁዋላ ጌታችን 12ቱን ደቀ መዛሙርቱን ወደ ደብረ ታቦር ወሰዳቸው: ዘጠኙን በእግረ ደብር (ከተራራው ሥር) ትቶ 3ቱን (ዼጥሮስን: ዮሐንስንና ያዕቆብን) ይዟቸው ወጣ እኒሕ ሐዋርያት "አዕማድ: አርዕስት: ሐዋርያተ ምሥጢርም" ይባላሉ::

➯በተራራው ላይ ሳሉም ድንገት የጌታችን መልኩ ከፀሐይ 7 እጅ አበራ: ከመብረቅም 7 እጅ አበረቀ "ወኮነ ልብሱ ጸዐዳ ከመ በረድ" እንዲል ከታቦር የተነሳው ብርሃነ ገጹ አርሞንኤም ደርሷል ያንን ተመልክተው መቆም ያልቻሉት ሐዋርያቱ ፈጥነው መሬት ላይ እንደ ሻሽ ተነጠፉ::

➯በዚያች ሰዓት ሙሴ ከመቃብር: ኤልያስም ከብሔረ ሕያዋን መጡ አንዳንዶቹ ጌታን 'ነቢይ' (ሎቱ ስብሐት) ብለውታልና ሙሴና ኤልያስ ተናገሩ:- "ስለ ምን አንተን ነቢይ ይሉሃል: እግዚአ ነቢያት - የነቢያት ፈጣሪ ነህ እንጂ" እያሉ ተገዙለት: አመሰገኑት::

➯ነገር ግን በቦታው ጸንተው መቆየት አልቻሉም መለኮታዊ ብርሃኑ ቢበዘብዛቸው ቅዱስ ሙሴም ወደ መቃብሩ: ቅዱስ ኤልያስም ወደ ማደሪያው በድንጋጤ ሩጠዋል::

➯በዚያች ሰዓት ሊቀ ሐዋርያት ጌታን "ሠናይ ለነ ኀልዎ ዝየ: ንግበር ሠለስተ ማሕደረ: አሐደ ለከ: ወአሐደ ለሙሴ: ወአሐደ ለኤልያስ - ጌታ ሆይ! በዚህ መኖር ለኛ መልካም ነው በዚህም 3 ዳስ እንሥራ አንዱን ላንተ: አንዱንም ለሙሴ: አንዱን ለኤልያስ" ብሎታል::

➯ቅዱስ ዼጥሮስ ለራሱ ሳያስብ ለጌታና ለቅዱሳን ነቢያቱ "ቤት እንሥራ" በማለቱ ሲመሰገን ጌታን የመጣበትን የማዳን ሥራ የሚያስተው ጥያቄ በማቅረቡ ከድካም ተቆጥሮበታል ለሁሉም ግን ሐሳቡ ድንቅና መንፈሳዊ ነው::

➯እርሱ ይሕንን ሲናገር መንፈስ ቅዱስ በደመና አምሳል ወረደና ከበባቸው አብ ከሰማይ ሆኖ "ዝንቱ ውዕቱ ወልድየ ዘአፈቅር: ወሎቱ ስምዕዎ - የምወደው: የምወልደው: ሕልው ሆኘ የምመለክበት የባሕርይ ልጄ እርሱ ነውና ስሙት" ሲል ተናገረ::

➯ደቀ መዛሙርቱም ከፍርሃት የተነሳ በዚያች ሰዓት እንደ በድን ሁነው ነበርና ጌታችን ቀርቦ ቀሰቀሳቸው በተነሱ ጊዜ ግን ሁሉም ነገር ወደ ነበረበት ተመልሶ ነበር:: (ማቴ. ማር. ሉቃ. )

➯በደብረ ታቦር የጌታችን ብርሃነ መለኮት ያዩ 3ቱ ሐዋርያት ብቻ አይደሉም:: እመ ብርሃን ካለችበት ሆና ስትመለከት 12ቱ ሐዋርያት ደግሞ በተራራው ሥር ሆነው በተደሞ ተመልክተዋል::

➯ይሕንን ድንቅ ብርሃነ መለኮት ያላየ ይሁዳ ብቻ ሲሆን እርሱም ስለ ክፋቱ የኢሳይያስ ትንቢት ተፈጽሞበታል ኃጢአተኛው የእግዚአብሔርን ክብር እንደማያይ ተነግሮበታልና:: "ያአትትዎ ለኃጥእ ከመ ኢይርዐይ ስብሐተ እግዚአብሔር" እንዲል (ኢሳ.)
ሊቁም የደብረ ታቦርን ምሥጢር ሲያደንቅ እንዲህ ብሏል:-

➯"ጸርሐ አብ ኪያከ በውዳሴ:
ወበርእስከ ጸለለ መንፈሰ ቅዳሴ:
አመ ገበርከ እግዚኦ በታቦር ምስለ ሐዋርያት ክናሴ መንገለ ሀሎ ኤልያስ ወኀበ ሐለወ ሙሴ ዘመለኮትከ ወልድ ከሠትከ ሥላሴ::"

➯ለወዳጆቹ ብርሃነ መለኮቱን የገለጠ ጌታ የእኛንም ዐይነ ልቡናችንን ያብራልን:: ከበዓሉ በረከትም ያሳትፈን::

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

https//t.me/AndEmnet ነሃሴ ፲፫ ቀን
August 18, 2026 233 2