ከታች ወደላይ እንዲወጡባት፣ ከላይ ወደታች እንዲወርዱባት እንደሚደረግ ሁሉ፣ አንቺም ለቃል ርደት፣ ለሥጋ ዕርገት ምክንያት ሆነሻልና ።
አንድም ዓርገ መባሉ ቅሉ ከሷ በነሳው ሥጋ ነውና።
አንድም ቅዱሳን ማረጋቸው ከሷ የነሳውን ሥጋ በኩር አድርገው ነውና።
“ዐርገ ከመ ያለቡ ዕርገተ ጸድቁን ንጹሐን እንዲል።”
አንድም ምዕራገ ጸሎት እንቺ ነሽ፤ ወብኪ የዐርግ ጸሎተ ኵሉሙ ቅዱሳን።
“አልቦ ጸሎት ወአልቦ ትንባሌ፣ እንበሌኪ ማርያም ዘየዓርግ ሉዓሌ” እንዲል።
“ወብኪ ተሐደሰ ቀዳሜ ኵሉ ፍጥረት”
ነፋስ፣ እሳት፣ ውኃና መሬት የሚባሉትን አራቱን ባሕርያት በያሉበት አምልከዋቸው ነበር። መመለካቸውን ብልየት፣ አለመመለካቸውን ተሐድሶ አድርጎ እንዲህ አለ።
“አንድም ከልጆቹ አስቀድሞ የነበረ አዳም የታደሰብሽ አንቺ ነሽ።”
ዕፀ በለስን በልቶ ብልየት አግኝቶት የነበረ አዳም በእመቤታችን ተሐድሶ ስለተገኘ ።
“አንድም ከፍጥረቱ ሁሉ አስቀድሞ የነበረ መልአኩ የታደሰብሽ አንቺ ነሽ።”
ቀውስጦስ የሚባል መልአክ አስታርቃለችና። ታሪኩ እንደምን ነው ቢሉ፣ ጌታ ሕፃናትን እንዲያጠፉ ብሎ መላእክትን ሰደደ። የእነዚህ ሕፃናት ዕዳቸው እንደምን ነው ቢሉ
በቅዳሴ ጊዜ ወዲያና ወዲህ እየተመላለሱ አውከው ነበር። ቀውስጦስ መልከ መልካም ሕፃን ከነማርዳው አገኘ። ለዝሰ ዘፈጠሮ ይቅትሎ(ይህንስ የፈጠረው ይግደለው) ብሎ ትቶታል።
የቀሩት መላእክት የተላኩበትን ፈጽመው ሲያርጉ እሱ ኃይል ተነስቶት ቀረ። አሻግሮ ቢያይ በደብረ ቀልሞን ዓምደ ብርሃን ተተክሎ አየ።
“ዛቲ መካን ትከውነኒ አራቂተ ምስለ እግዚእየ” ብሎ ተጎትቶ ሂዶ ከደጀ ብርሃን ወደቀ። ዲያቆኑም ለተልዕኮ ሲገባ ከዚያ ወድቆ አገኘው። አንተ ምንድን ነህ ምድራዊ ነህ ሰማያዊ አለው። ግብሬ ምድራዊ አድርጎኝ ነው እንጂ ተፈጥሮዬስ ሰማያዊ ነው አለው።
አሁንም ሂደህ ለአባ ሳሙኤል ንገርልኝ አለው። ሂዶ ነገረው። እሱም መጥቅእ መትቶ ሕዝቡን ሰብስቦ ፵፩ እግዚኦታ ፵፩ በእንተ ማርያም አድርሶ ሄዶ ከሥዕለ ማርያም ተማፀነ።
በቀኝ እጅህ ቀኝ ክንፉን በግራ እጅህ ግራ ክንፉን ይዘህ ተንሥእ በስመ እግዚአብሔር ፈጣሪከ በለው አለችው።
ሂዶ በቀኝ እጁ ቀኝ ክንፉን በግራ እጁ ግራ ክንፉን ይዞ ተንሥእ በስመ እግዚአብሔር ፈጣሪከ በለው።
የቀደመ ኃይሉ ተመለሰለት። በረድኤት እንዳልለያችሁ ስሜን ከአባ ሳሙኤል አትለዩት ብሏቸው አርጓል።
“ርኅራኄኪ ማርያም ቀሲፈ ሕፃን አኅደጎ። ለመልአከ ብኪ ዘተማኅፀነ ትእዛዘ ጽጌኪ በአንትጎ።
እምድጎረ ተስዕኖ በአንትጎ።
ዐሪግ ለቀዊም ኅበ ይዛወጎ።”
ሳሙኤል ሶበ ጸለየ ደብረ ቀልሞን ዐሪጎ፣ኃይለ ተአምር ዘሥዕልኪ፣ ሰማየ መዘጎ እንዳለ ደራሲ።
ሰአሊ ለነ ቅድስት።
ከቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ የተወሰደ