"ኢትዮጵያን ከወጣቶቿ ነጥሎ ማየት አይቻልም!"
ኢትዮጵያን ከወጣቶቿ ነጥሎ ማየት እንደማይቻል የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ የወጣቶች አብላጫ ዕድሜ ስብጥር ለሀገር ብልጽግና መረጋገጥና መጽናት ታላቅ ዕድል መሆኑን አሳሰቡ።
የኢትዮጵያ ወጣት መልካም ዓላማን አንግቦ የሚንቀሳቀስ፣ የለውጥ ዋነኛ ሞተርና የሉዓላዊነት ጽኑ ማገር መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ወጣቱ ትውልድ የሀገሩን ታሪክ በአዲስ ብዕርና ብራና እየጻፈ እንደሚገኝ ጠቁመው፣ ሀገራችንን የኋሊት ጠፍንገው የያዟትን አጓጉል ልማዶች፣ አላስፈላጊ ንትርኮች፣ ጭቅጭቅ እና ግጭቶች በመራቅ አሁን ያለው ወጣት በልማት ላይ አተኩሮ ድህነትን እንደተጠየፈ ገልጸዋል።
የመደመር መንግሥትም የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትና የአመራርነት ሚና ለማጠናከር በትኩረትና በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝ አስታውሰዋል።
በመጨረሻም ሀገራዊ ርዕይን ዕውን ለማድረግ ሁሉም በንቃት እንዲተጋና በፍቅር እንዲመላለስ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት ጥሪ አቅርበዋል።

August 12, 2026 192