የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉዞ በወፍ በረር
ነሐሴ 20/2018 ዓ.ም
ኢትዮጵያዊያን ለበርካታ ዘመናት የሃሳብ ልዩነቶቻንን በውይይት ከመፍታት ይልቅ የኃይል አማራጮችን ስንጠቀም ከርመናል። እነዚህ አማራጮች በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የተፈጠሩ አለመግባባቶችን በማባባስና ግጭቶችን በማፋፋም ከፍተኛ ሰብአዊ እና ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ እንዳስከተሉ የታሪክ መዛግብት እማኝ ናቸው።
የሃይል አማራጭ ያስከተለውን ዘመን ተሻጋሪ ኪሳራ የተረዳው የዚህ ዘመን ትውልድ በሀገራችን ኢትዮጵያ ዘመናትን የተሻገሩ ችግሮች መፍትሔ እንደሚያስፈልጋቸው በማመን የሀገራዊ ምክክር ሃሳብን ቀስ በቀስ በማጎልበት ወደ ተግባር ምዕራፍ አድርሶታል፡፡ ትውልዱ ከሀሳብም ወደ ተቋም አሸጋግሮታል፡፡
👉ከሃሳብ ወደ ተቋም
በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር እንዲካሄድ ፍላጎት የመጣው ከአንድ ወገን ብቻ አልነበረም። የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማህበራት፣ የሀገር ሽማግሌዎች መማክርት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በሀገሪቱ ውስጥ የሚስተዋሉትን ያለመግባባት አዙሪቶች በምክክር የሚፈቱበት መድረክ እንዲመቻች ለበርካታ ጊዜያት ሲወተውቱ ቆይተዋል። ከዚህ ባሻገር እነዚህ አካላት በሌሎች ሀገራት ከተካሄዱ የሀገራዊ ምክክር ተሞክሮዎች ትምህርት በመውሰድ፣ ምክክር ወደ መግባባት ሊያደርስ የሚችል አዋጭ መንገድ እንደሆነ በመገንዘብ መንግስት እርምጃ እንዲወስድ አበረታተዋል፤ ጠይቀውማል፡፡
ይህ ሂደት በተለይም በታህሳስ ወር 2014 ዓ.ም በሀገሪቱ የምክክርን መሰረት በመጣል ረገድ አንድ እርምጃ ተራመደ፡፡ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንን በማቋቋም የሀገራዊ ምክክር ሂደቱን እንዲመራና እንዲያስተባብር ኃላፊነት ሰጠው።
የኮሚሽኑ አመሰራረት በራሱ የሕዝብ ተሳትፎን ባማከለ መልኩ የተቃኘ ነበር፡፡ ከሕዝብ በቀረበው ጥቆማ መሠረት 632 ዕጩዎች ለኮሚሽነርነት ተጠቁመው፣ 42ቱ በዕጩነት ከተመረጡ በኋላ፣ በመጨረሻም 11 ኮሚሽነሮች ተመርጠው ተቋሙን እንዲመሩ ቃለ መሐላ ፈጸሙ።
👉የሂደቱን መሠረት መጣል
የኮሚሽኑ የመጀመሪያ ተግባር በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በአንድ አዳራሽ ውስጥ መሰብሰብ አልነበረም፡፡ ይልቁንም የምክክር ሂደቱ ትርጉም ያለው እንዲሆን መደላድል መፍጠር ነበር፡፡ በመሆኑም ኮሚሽኑ በመጀመሪያ ሥራው እጅግ መሰረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያሉ የአለመግባባት መንስኤዎችን ለመለየት፣ እነማን መሳተፍ እንዳለባቸው ለመወሰን እና ኢትዮጵያውያን ለምክክር የሚሆኑ ጉዳዮችን በማዋጣት ረገድ እንዴት አስተዋፅኦ ማበርከት እንደሚችሉ የሚያስችል ሥነ-ዘዴ አዘጋጀ፡፡ በሂደቱ በወረዳ ደረጃ ከሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ጀምሮ እስከ ፖለቲካና የሃሳብ መሪዎች፣ የመንግስት ተቋማት፣ ማህበራት እና በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በማካተት የሰፊ ባለድርሻ አካላት ስብስብን ለየ፡፡
በክልሎች/ ከተማ አስተዳደሮች የተካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ከፖለቲካ እና ከተቋማት ወሰን የተሻገረ እንዲሆን ተደርጎ የተቃኘ ነበር፡፡ የአርሶ/አርብቶ አደር ተወካዮች፣ የንግዱ ማህበረሰብ፣ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ እድሮች፣ የማህበረሰብ መሪዎች፣ የመንግስት ሰራተኞች፣ መምህራን፣ በባህል እና በሙያቸው ምክንያት የተገለሉ እንዲሁም ተፈናቃዮች በክልል እና በከተማ አስተዳደር ደረጃ በተካሄዱ ሂደቶች ተሳታፊዎች ሆነዋል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የመንግስት ተወካዮች፣ ተቋማት እና ታዋቂ ግለሰቦችም እንደ ቁልፍ ባለድርሻ አካላት ተሳታፊዎች ሆነዋል፡፡
በፌዴራል ደረጃ 38 የባለድርሻ አካላት ቡድኖች በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ የነቃ ተሳትፎ አድርገዋል፡፡ በዚህ ሂደት በተለይም የሃይማኖት ተቋማትን፣ የዲሞክራሲ ተቋማትን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ የሲቪል ማህበራትን፣ የመንግስት አካላትን፣ ሀገር አቀፍ ማህበራትን፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን እና የሚዲያ ተቋማትን የወከሉ ወኪሎች ተሳታፊዎች ሆነዋል፡፡
በሌላ በኩል ኮሚሽኑ በአፍሪካ፣ ሰሜን አሜሪካ፣ መካከለኛው ምስራቅ እና አውሮፓ ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን አጀንዳ አሰባስቧል፡፡
👉ሀገራዊ አጀንዳ መቅረፅ
የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራው እንደተጠናቀቀ ኮሚሽኑ የሰበሰባቸውን አጀንዳዎች መቅረፅ እና ለምክክር ሂደቱ የማዘጋጀት ሥራ አከናወነ፡፡ ይህንን ተከትሎ ረቂቅ አጀንዳዎች ለሃይማኖት ተቋማት፣ ለሲቪክ ማህበራት፣ ለፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ለመንግስት አካላት፣ ለምሁራን እና ለሌሎች ባለድርሻ አካላት ግብዓት እንዲሰጡባቸው ቀርበው ሁሉም አካላት የበኩላቸው አበርክተዋል፡፡ ይህ ሂደት የተቀረፁ የምክክር አጀንዳዎችን ለማጥራት ብቻ ሳይሆን፣ ባለድርሻ አካላት ሃሳቦቻቸው በሂደቱ ውስጥ መንፀባረቃቸውን በማረጋገጥ ወደ ሀገራዊ መግባባት ሊያደርሱ የሚችሉ ርዕሰ ጉዳዮችን በመቅረፅ ረገድ አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ዕድል ሰጥቷል፡፡
👉ኢትዮጵያዊያንን ወደ ምክክር መድረክ ማሰባሰብ
ከየወረዳው ከሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች፣ ከክልል እና ከተማ አስተዳደሮች ባለድርሻ አካላት፣ ከፌዴራል ባለድርሻ አካላት እና ከዲያስፖራው የተውጣጡ 4000 ኢትዮጵያዊያን ተሳታፊዎች በአንድ ላይ ለመመካከር ተሰባሰቡ፡፡ እነዚህ ተሳታፊዎች ኮሚሽኑ ቀደም ሲል አጀንዳዎችን ካሰባሰበባቸው አካላት እና ባለድርሻ አካላት የተመረጡ ወይም የተወከሉ ሲሆኑ ይህም በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለውን ውክልና ከቀደሙት የምክክር ሂደቶች ጋር በአግባቡ ያጣመረ ነበር፡፡
የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ዓላማ ኢትዮጵያውያን እጅግ መሰረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮቻቸው ላይ የሚመካከሩበት፣ የተሻለ መግባባትን የሚያጎለብቱበት፣ የጋራ መግባባት የሚደረስባቸውን አቅጣጫዎች የሚለዩበትን መድረክ መፍጠር ነበር፡፡ በጥቅሉ ሂደቱ ምክክርን የአለመግባባቶች መፍቻ የማዕዘን ድንጋይ የማድረግ ጥረት ነበር፡፡
👉ምክክርን ማዕከል ያደረጉ ሃሳቦች
የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም በይፋ የተጀመረ ሲሆን ሂደቱ 4,000 ተመካካሪዎችን ከሁሉም የሀገራችን እና የዓለማችን ክፍሎች ማሰባሰብ ችሏል።
በሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ምክክር የሚደረግባቸው ስምንት ሀገራዊ አጀንዳዎች የተለዩ ሲሆን እያንዳንዱ 500 አባላት ያሉት ተመካካሪ ቡድን በአንድ አጀንዳ ላይ ሲመካከር ሰንብቷል፡፡
ጉባኤው የተመራበት ሥነ-ዘዴም ተመካካሪዎች የመናገር፣ የመደማመጥ እና የመግባቢያ ነጥቦችን የመለየት ዕድል እንዲኖራቸው በሚያስችል መልኩ ነበር። ከዚህ ባሻገር የምክክር ሂደቱ 10 አባላት ባሏቸው ትንንሽ ቡድኖች ተጀምሮ፣ 50 አባላት ወዳሏቸው ንዑሳን ቡድኖች፣ በመቀጠልም 250 አባላት ወዳሏቸው ስልታዊ ቡድኖች አድጓል።
በምክክር ሂደቱ የቀረቡ ምክረ-ሀሳቦች ከላይ በተጠቀሱት መንገዶች ምክክር ተደርጎባቸው ከተጣሩ በኋላ የተጠቃለሉ ምክረ-ሃሳቦች 500 አባላት ባሉት የአጀንዳ ተመካካሪ ቡድን ቀርበው ፀድቀዋል። እያንዳንዱ ተመካካሪ ቡድን በመጨረሻም በተለያዩ አጀንዳዎች መካከል የቀረቡ ምክረ-ሃሳቦችን ማጣጣም (cross-validation) ለማካሄድ 15 ተወካዮችን መርጧል፡፡ በዚህ መሰረት በአጠቃላይ 120 የሚሆኑ የምክረ-ሃሳብ አቀናጆች ተመርጠው ሥራቸውን በአግባቡ አከናውነዋል፡፡ በሂደቱ ምክረ-ሃሳቦችን የማጣጣም ዋነኛ ዓላማም በተለያዩ ተመካካሪ ቡድኖች ውስጥ የተነሱ ምክረ-ሃሳቦች እርስ በእርስ እንዳይጣረሱ እና አላስፈላጊ ድግግሞሽ እንዳይኖር በማሰብ ነበር፡፡
August 26, 2026 53