Afar Communication Bureau: post #5187 — TG.ME

Afar Communication BureauPhoto
ይህ ጉባኤ ስኬታማ ይሆን ዘንድ በተለያዩ ዘርፎች ሙያዊ እገዛ ያደረጉ ባለሙያዎች መኖራቸው ሊዘነጋ አይገባም። 80 የባለሙያዎች ቡድን ለተሳታፊዎች በአጀንዳዎቹ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥቷል፤ ይህም ተሳታፊዎች መረጃን ማዕከል ያደረገ ምክክር እንዲያደርጉ ትልቅ ሚና ተጫውቷል፡፡

ከዚያ በተጨማሪ 160 የሚጠጉ አመካካሪዎች የምክክሩን ሂደት የመሩ ሲሆን፣ 158 ቃለ-ጉባኤ አዘጋጆች (rapporteurs) በእያንዳንዱ የምክክር ሂደት ውስጥ የነበሩ ምክረ-ሃሳቦችን በመሰነድ ለሂደቱ መሳካት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርገዋል።

👉ከመግባባት ያለፈ ሀገራዊ ምክክር

የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ፋይዳ ምክረ-ሃሳቦችን በመግባባት ማዘጋጀት ብቻ አልነበረም። ከዚያ በተጨማሪ የተለያየ ልምድ፣ ፍላጎት እና የፖለቲካ አቋም ያላቸው ሰዎች እርስ በእርስ በቀጥታ የሚነጋገሩበትን መድረክ መፍጠርም ጭምር ነበር፡፡

ይህ መድረክ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል ውስጥ ትልቅ ሽግግርን ያመለክታል፦ የሂደቱ ግብ "ማን አሸነፈ፣ ማን ተሸነፈ?" ከሚለው ኋላ ቀር እሳቤ ይልቅ ወደ "በምን ላይ መስማማት እንችላለን? ምን አይነት ልዩነቶችን ማስተናገድ ይቻላል? እና በአንድነት ምን አይነት የጋራ ተስፋ መገንባት እንችላለን?" ወደሚለው ጥያቄ መሸጋገር ነው፡፡

👉የመዝጊያ ሥነ-ሥርዓት

ነሐሴ 16 ቀን 2018 ዓ.ም በተካሄደው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው የመዝጊያ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴን ጨምሮ ጥሪ የተደረጋላቸው የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገራት የክብር እንግዶች ተገኝተው የተለያዩ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል፡፡ በመድረኩ ላይ ፕሬዚዳንት ታዬ እንደተናገሩት ሀገራዊ ምክክሩ አንድነትን የሚያጠናክር ትልቅ የታሪክ ምዕራፍ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

በሌላ በኩል በክብር እንግድነት የተገኙት የቀድሞው የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፣ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተወጣጡ ወኪሎች እርስ በእርስ ለመግባባት ያሳዩትን ተነሳሽነት አድንቀው ይህም ዜጎች በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ ለመነጋገር ፈቃደኛ ሲሆኑ የበለጠ ፍሬያማ እንደሚሆን አውስተዋል፡፡

የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ምክክር የሀገሪቱን ፈተናዎች ለመፍታት የሚያስችል አቅም ያለው መንገድ መሆኑን ጠቁመው ኢትዮጵያ በምክክር ልትፈታው የማትችለው ምንም ዓይነት ፈተና እንደሌለ አፅዕኖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡ አክለውም በኃይል አማራጭ አሸናፊ የሚሆን አካል እንደማይኖር ገልፀው ምክክር ሁሉንም አሸናፊ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።

ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገብረሥላሴ በበኩላቸው የሀገራዊ ምክክሩ መጠናቀቅ በኢትዮጵያ የፖለቲካ እና የማህበራዊ ጉዞ ውስጥ ትልቅ ምዕራፍ መሆኑን ገልጸዋል። ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ አክለውም ሀገራዊ ምክክሩ ኢትዮጵያውያን ለረጅም ጊዜ የቆዩ ቅሬታዎችን፣ የፖለቲካ ልዩነቶችን እና የታሪክ ክፍፍሎችን ከግጭት ይልቅ በምክክር እንዲፈቱ ዕድል የፈጠረ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

👉የነገው መንገዳችን

የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ከአንድ ወቅት ክስተት ባላፈ የሚሻገሩ ታላላቅ ግቦች አሉት፡፡ በዚህ ሂደት የሚጠበቁ ውጤቶች መሰረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባትን መፍጠር፣ ሀገራዊ አንድነትን እና ማህበራዊ ትስስርን ማጠናከር፣ የመፍትሔ ሃሳቦች የሕዝብ ባለቤትነት እንዲኖራቸው ማድረግ፣ በተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች መካከል እምነትን መገንባት እና ለዘላቂ ሰላም፣ ለዲሞክራሲያዊ አስተዳደር እና ለሀገር ግንባታ መሠረት መጣልን ያካትታሉ፡፡

የሀገራዊ ምክክር ጉዞ ረጅም ነበር። ተቋም መፍጠርን፣ ሥነ-ዘዴን ማዘጋጀትን፣ ባለድርሻ አካላትን መለየትን፣ አጀንዳ ማሰባሰብን፣ የሕዝብ ተሳትፎን ማጎልበት፣ ውክልናን ማረጋገጥ፣ አጀንዳን መቅረፅን እና በሀገር አቀፍ ደረጃ የምክክር ጉባኤ ማካሄድን ጠይቋል፡፡

በሀገራችን ኢትዮጵያ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በአንድነት መቀመጥ፣ መደማመጥ እና የጋራ መግባባትን መፈለግ በራሱ ትልቅ እርምጃ ነው።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የኢትዮጵያ ልጆች ሀገራዊ ችግሮችን በምክክር መፍታት እንደሚችሉ ያስመሰከሩበት መድረክ!

በምክክር ሁሉም አሸናፊ ነው!
August 26, 2026 56