ቃ ላ ት | 𝚀 𝚊 𝚕 𝚊 𝚝: post #40 — TG.ME

ዘመናችን በወል የታመምንበት ነው። ስብራታችን፣ ውድቀትና መከራችን እንደ ትውልድ በለጋው እድሜያችን ልክ የተሰፋ አይመስልም። የዘመን ተጋሪያችን ወጣቱ ደራሲ እሱባለው አበራ ያለንበትን ምስቅልቅል አውድ ሊፈክር የምናብ ጸጋን ለብሶ በቃል ኪነት የኖረውን ሕይወት ወርድና ቁመት መትሮ እንደ ግለሰብ፣ እንደ ማኅበረሰብና እንደ ሀገር የጠራ ምስላችን እንዲህ ያለ ነው ሊለን መጥቷል። ሙከራው ፍፁም ኪናዊ ነው። የምርመራ ቀስቱ ውጫዊ ብቻ ሳይሆን ወደ ውስጥም ነው። ጥቁምታው ወደ 'እነርሱ!' ብቻ ሳይሆን ወደ 'እኛም!' ጭምር ነው። ተጠየቁ ላንተና ላንቺ ብቻ ሳይሆን ለእኔም ነው። ኀሠሣው ከቤተሰብ፣ ማኅበረሰብና ሀገር አውድ ቢነሣም የተሰፋው በሰው ልክ ነው። እሱባለው “ፀሓይ ከጨለማዬ ምን አለሽ?” ብሎ በሰየመው ሁለተኛው ወጥ የልብ ወለድ ሥራው (novel) የማኅበረሰብን ነገረ ሰብዕ፤ ቅስም ሰባሪ ቁልቁል ጉዟችንን፤ ሳይጠና የተሰበረን፣ ሳያብብ የተቀጨን ትውልድ አራራይ ሥነ ጽሑፍ ባስታጠቀው ኪናዊ ማጥለያና ከሀገሩ ሊቅ ሙዚቃዊ ድርሰት ባለመደው አዲስ የጽሑፍ ቅርጽ አሽቶ የበሽታችንን ልብ አልቆ ነግሯል። ከበኩር ሥራው “ትዝታሽን ፡ ለእኔ ፥ ትዝታዬ ፡ ለአንቺ” በተለየ አዲስ ሙከራን ይዞ የመጣበት የተዋበ ድርሳን ነውና ቃላት መጽሔት ለባልንጀራችን እሱባለው እንኳን ለዳግም ህትመት በቃህ እያልን መጽሐፉ ነገ ዕለተ ረቡዕ ለንባብ ስለሚበቃ ለቃላት መጽሔትና ፖድካስት ቤተሰቦች በተገኘበት እንዲነበብ ጋብዘናል።

❤50👍5😢1
January 16, 2024 6.6K 9