< እንዴት ሞተች እንጂ እንዴት ተነሣች ብለኽ አትገረም! >
ከሰው ኹሉ መርጦ እናቱ ያደረጋት ጌታ፥ ከሰው ኹሉ መርጦ ከሞት አሥነሳት፤ አሳረጋት፡፡ ከሰው ኹሉ ተመርጣ ሰማይና ምድር የማይችሉትን ጌታ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ጸንሳ ወልዳው የለምን? ከተገረምክ በዚኽ ተገረም፡፡
እናት ኾና ድንግል፥ ድንግል ኾና እናት መኾን የምትችል ሴት በምድር ላይ አልነበረችም፤ ወደፊትም አትኖርም፡፡ ቅድስት ድንግል ማርያም ግን በዐለም ያሉ ሴቶች ኹሉ የማይኾኑትን ኾነች፡፡ ድንግልም እናትም፡፡ ከትንሣኤዋ ይልቅ ይኽ አይደንቅምን?
የክብር ትንሣኤና ዕርገትማ በሃይማኖትና በምግባር ለጸኑ ሰዎች ኹሉ ጊዜው ሲደርስ ይፈጸምላቸዋል፡፡ይነሣሉ ያርጋሉ፡፡ ከአንስተ ዐለም ተለይታ አምላኳን ልጄ ብላ መጥራት የቻለች የሕይወት እናት፥ መሞቷ እንጂ መነሣቷ ምን ይገርማል??
ሙሴ በሲና ያያት ዕፅ፥ ቀርበው ካላይዋት በስተቀር እሳት ያቃጠላት ትመስላለች፡፡ እንደሙሴ ቀርቦ ለተመለከታት ግን እሳት ቢነድባትም ዕፀ ጳጦሷ አትቃጠልም፡፡ ይኽ እሳት የመለኮት ምሳሌ ኾኖ በሊቃውንቱ ተተርጉሞ ነበር፡፡ ዛሬ ግን እሳቱ የሞት ምሳሌ ኾኖ ይገለጣል፡፡ እሳት ያላቃጠላት ቅጠል ደግሞ እመቤታችን ናት፡፡
ዳሩ ይኽን ለመረዳት ወደደብረ ሲና መውጣት ብቻም አይጠቅምም፡፡ እንደ ሙሴ ጫማንም ማውለቅ ይበጃል፡፡ ሊቃውንቱ፥ "ሙሴ የለበሰው ጫማ ከሞቱ እንስሳት ቆዳ የተሠራ በመኾኑ ያን ተጫምቶ እንዳይቀርብ ተከለከለ" ብለው ተርጉመዋል፡፡
የሞቱ እንስሳት ቆዳ ውጤት የኾነው ጫማ፥ ሙታነ ሕሊናን ይወክላል፡፡ ጌታችን ክርስቶስ በእናቱም ለእናቱም ያደረገውን ድንቅ ነገር የማያምን ልብ፥ የሙሴ ጫማ ነው፡፡ መውለቅ አለበት፡፡ እግርን ሳይኾን ዐይንን የሚጋርድ ግርዶሽ ነውና፡፡
ዕፀ ጳጦስ የተባልሽ ድንግል ኾይ፥ጫማችንን የፈታን ሙሴዎች ኾነን ክብሩን እናይ ዘንድ ለምኝልን!
© ሊቀ ሊቃውንት ሥሙር አላምረው
በድጋሜ እንኳን አደረሳችኹ!